You are currently viewing የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ አላማጣ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው

የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ አላማጣ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው

Photo- FILE

ዋዜማ-ከሦስት ወራት ገደማ ወደ አወዛጋቢዎቹ የራያ አካባቢዎች የገቡ ታጣቂዎች ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብት ያላቸው ምንጮች ሰምታለች፡፡

ታጣቂዎቹ ከተቆጣጠሯቸው እንደ ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም፣ ዛታ፣ ዋጃና ጥሙጋ ካሉ አካባቢዎች ለቀው እንዲወጡ የታዘዙት በፌደራል መንግሥት ነው ተብሏል፡፡ ታጣቂዎች የሚወጡት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ታጣቂዎች ከአካባቢዎቹ ወጥተው ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡

የትግራይ ታጣቂዎች ለወራት ተቆጣጥረዋቸው ከቆዩ የራያ አካባቢዎች ጠቅልለው እንዲወጡ እስከ ሰኔ 30/2016 ድረስ ቀነ ገደብ እንደተሰጣቸው ምንጮች ጠቁማዋል፡፡ በአካባቢዎቹ የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አካላት የትግራይ ታጣቂዎች በተጠቀሰው ቀነ ገደብ ውስጥ ለቀው እንዲወጡ እንዲያደርጉ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የትግራይ ታጣቂዎች ለቀው ሲወጡ የጦር መሳሪያ ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ኃይል እንዳይኖር በአካባቢው የተሰማራው የፌደራል ጸጥታ ኃይል ሀላፊነት መውሰዱን ተረድተናል፡፡ ውሳኔው የተላለፈው የፌደራል መንግሥት የአወዛጋቢ አካባቢዎችን ጉዳይ ለመፍታት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት አካባቢውን ከሁለቱም ወገኖች የታጠቀ ኃይል ነጻ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡

ይሄንኑ ተከትሎ የትግራይ ታጣቂዎች ከሰኔ 25/2016 ጀምሮ ከዋጃ እና ጥሙጋ አንዳንድ አካባቢዎች መውጣት ጀምረዋል፡፡ ከተጠቀሱት አካባቢዎች የወጡት ታጣቂዎች ከአላማጣ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ “አየር ማረፊያ” ተብሎ በሚጠራ ቦታ ላይ መሰባባቸውን የአካባቢው የዐይን እማኞች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በአላማጣ ከተማ ግን እስከ ሰኔ 26/2016 ከስዓት ድረስ ታጣቂዎች  ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን ዋዜማ ከከተማዋ ነዋሪዎች ሰምታለች፡፡

በአላማጣ ከተማ የሚገኘው የፌደራል ጸጥታ ኃይል ሰኔ 26/2016 ለማኅበረሰቡ ባስተላለፈው መመሪያ የባጃጅ እንቅስቃሴ ከቀኑ 12 ስዓት በኋላ መከልከሉን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

በመመሪያው የሰው እንቅስቃሴ፣ ምግብ ቤቶችና መዝናኛ ቤቶች አገልግሎት ከምሽት ኹለት ስዓት በኋላ አንዳይኖር ተገድቧል፡፡ እንደ ጩቤ ያሉ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ጨምሮ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ መከልከሉን ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ቀድም ሲል ከታጣቂዎች ጋር አብረው የገቡትንም ይሁን በቀጣይ የሚገቡትን ተፈናቃዮችን እንዳይተናኮል በመመሪያው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ በተፈናቃዮች ላይ ማንኛውንም አይነት ትንኮሳ የሚፈጽም አካል ላይ የፌደራል ጸጥታ ኃይሎች እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል፡፡ በተጨማሪም ያለ መከላከያ ሰራዊት እና ፌደራል ፖሊስ ፈቃድ ማንኛውም አካል ስብሰባ እንዳይቀመጥ በክልከላ መመሪያ ላይ ተጠቅሷል፡፡

ታጣቂዎች ከአካባቢዎቹ እንዲወጡ በሰላማዊ ሰልፍ ሲጠይቅ የነበረው ማኅበረሰብ ባለፈው እሁድ ሊያደርግ የነበረውን ሰልፍ  ተከልክሏል። በአካባቢው የተሰማራው የፌደራል ጸጥታ ኃይል አዛዦች ሰልፉ አንዳይደረግ የከለከሉት “ታጣቂዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ስለተሰጣቸው ሰልፉ አስፈላጊ አይደለም” በማለት ነው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ በጠለምት በኩል ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው መመለስ ሲጀምሩ፣ የትግራይ ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋቸው ከቆዩ ቦታዎች እየወጡ መሆኑ ተሰምቷል። ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው መመለስ መጀመራቸውን ተከትሎ የትግራይ ታጣቂዎች ከምሥራቅ ጠለምት ሦስት ቀበሌዎች መውጣት መጀመራቸውን የመከላከያ ሰራዊት ምንጮች ነግረውናል።

በጠለምት በኩል የፌደራል መንግሥቱን አቅጣጫ የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል በርሃኑ በቀለ በጉዳዩ ላይ ለኢቲቪ በሰጡት ማብራሪያ  ይህን አረጋግጠዋል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለሱ እና የትግራይ ታጣቂዎችን የማስወጣት አፈጻጸሙ ጎን ለጎን እየተፈጸመ መሆኑንም ጠቁመዋል። [ዋዜማ]

The post የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ አላማጣ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው first appeared on Wazemaradio.

The post የትግራይ ታጣቂዎች ከራያ አላማጣ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጣቸው appeared first on Wazemaradio.

Source: Link to the Post

Leave a Reply