የትግራይ ኃይል ታጣቂዎችን ያለበቂ ስልጠና ወደ ፖሊስና ማረሚያ ቤት ስራዎች ማስገባት ለእረኞችና ተጠርጣሪዎች ስጋት ነው- ኢሰመኮ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ ደቡብ ዞን፣ ደቡብ ምስራቅ ዞን እንዲሁም በመቀሌ ልዩ ዞን በሰብዓዊ ሁኔታዎች እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ  ከሰኔ 30 ቀን  2015 እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2015 የተደረገ ክትትልን በ40 ገጽ ሪፖርት ዛሬ የካቲት 12 ቀን 2016 ይፋ አድርጓል። 

ኢሰመኮ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላም በትግራይ ክልል በኤርትራ መከላከያ ሠራዊት እና በአማራ ኃይል ቁጥጥር ስር ከሚገኙት አካባቢዎች የወጡ አንዳንድ ሰዎች የወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብሏል። 

አብዛኛዎቹ የጥቃቶቹ ሰለባዎች በክልሉ የጤና ዘርፍ አጠቃላይ ሁኔታ የህክምና፣ የስነ-ልቦና፣ የህግ እና የመልሶ ማቋቋም አገልግሎቶች ወሳኝ እጥረት ያጋጠማቸው በመሆኑ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። በተጨማሪም ከወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃት የተረፉ ሰዎች ከማህበረሰቡ ዘንድ መገለል ደርሶባቸዋል የተባለ ሲሆን ይህም ብዙዎች መሰል ጥሰቶችን ከማጋለጥ እንዲቆጠቡ እና ህክምና እንዳይፈልጉ ማድረጉን ኢሰመኮ አሳስቧል።         

በትግራይ ክልል የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች የመጠለያ እና የጤና አገልግሎትን ጨምሮ ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች በጣም የጎደሉ እና የማይመጥኑ እንደሆኑ ሪፖርቱ አመላክቷል። ለዘጠኝ ወራት ገደማ ከዋና ዋና ደጋፊዎች ተቋርጦ የቆየው እርዳታ ችግሩን አባብሶታልም ሲል ኢሰመኮ ገልጿል። 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በክልሉ እየታየ ያለው “የሰብዓዊ መብት ሁኔታ መሻሻልን” በደስታ ተቀብለው “ሰብዓዊ ስጋቱን ለመቅረፍ እና ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት ጠቃሚ ቢሆንም ከወሲባዊ እና ጾታዊ ጥቃቶች የተረፉ ሰዎችን በተቀናጀ ሁኔታ መደገፍ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

“የጤና እና የትምህርት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ማስጀመር እና የሕግ ማስከበር ስርዓቶችን መመለስ በክልሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አጽንዖት መስጠታቸውን አዲስ ማለዳ ከኮሚሽኑ ሪፖርት ተመልክታለች። 

በትግራይ ክልል የማረሚያ ቤቶችና የፖሊስ አገልግሎቶችን እንደገና ወደ ተግባር ለማስገባት አበረታች ጥረት ቢኖርም፤ በፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳትና ዘረፋ፣ እንዲሁም የሰው ኃይል እጥረት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት አሁንም ፈተና ሆኗል ተብሏል። 

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳስታወቀው የቀድሞ የትግራይ ኃይል ታጣቂዎችን ወደ መደበኛ ፖሊስ እና የማረሚያ ቤት ሥራዎች ያለ በቂ ሥልጠና ማስገባት፤ በቁጥጥር ስር በሚውሉ እና በእስረኞች ጥበቃ ላይ ስጋት ይፈጥራል። ኮሚሽኑ አክሎም እንደ ምግብ፣ ውሃ እና ህክምና ያሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች እና አቅርቦቶች እንዲሁ በማረሚያ እና እስር ቤቶች በቂ አልነበሩም ብሏል።

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ የሠላም ስምምነቱ በፌዴራል መንግስት እና በክልል አስተዳደሩ አስፈጻሚዎች መካከል መደበኛ ግንኙነት እንዲጀምር እንዲሁም ጤና እና ትምህርትን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ወደነበረበት ለመመለስ የተጀመሩ ጥረቶች እንዲቀጥሉ አስችሏል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ በጦርነቱ የተስተጓጎለውን ትምህርት ለማካካስ በአንድ ዓመት ውስጥ ውስጥ የሁለት ዓመት ትምህርት ለማስተማር የጀመረው ስራ የሚበረታታ ነው የተባለ ሲሆን ኢሰመኮ ይህ አሰራር በድህረ ጦርነት ወቅት የተለመደ ነው ብሏል።

ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች ግን ከጦርነቱ በኋላ ወደ ትምህርት ስርዓቱ የተመለሱ ተማሪዎች እና መምህራን ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች። ከጥቅምት 29 ቀን 2016 እስከ ሕዳር 10 ቀን 2016 ድረስ የመልሶ ፍተሻ በኮሚሽኑ የተካሄደ ሲሆን ዉጤቱ በሌላ ሪፖርት ይፋ ይደረጋል ተብሏል።

Source: Link to the Post

This Post Has One Comment

  1. Tesfa

    የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ እኮ ነው። ችግሩ የስልጠና ጉዳይ ብቻ አይደለም። የሰው ልቦና በዘርና በቋንቋ የተማሰ በመሆኑ ጭራሽ በህግ ለመኖርና ለማኖር አይችልም። በዚያም ላይ እልፎች ሲሞቱና ሲገደሉ ያዪና የገደሉ ሁሉ የጭንቅላት በሽታ ያለባቸው በመሆኑ ጤነኛ ሆነው በጤና በህብረተሰብ መካከል ይኖራሉ ማለትም ከባድ ነው። ስንት ግፍ ፈጽመዋል? ስንት ግፍ ተራምደው ሄደዋል? ማንም ሰው ጭንቅላቱን ተቆርጦ ቁሞ ሲሄድ ያየነው እስከ አሁን የለም። እነዚህ ስብስቦች እኮ የቁም ሙቶች ናቸው። ሰላምን አያውቋትም። እንዲያውቋትም ገና ከጅምሩ አልተፈቀደላቸውም። ይቅርና በሃገር ቤት ተሰደው ከውጭ ከወጡ በህዋላ እንኳን ይህ የዘር ጥላቻቸውና መቧቀሳቸው ይብስባቸዋል እንጂ አልተሻላቸውም። በየሃገሩ ሰውን በደቦ የሚደበድቡ፤ ልብ ያላቸውን የትግራይ ተወላጆች በፓለቲካ ልዪነት ከሥራቸው ለማፈናቀል የውሽት የክስ ደብዳቤ የሚያስገቡ፤ ሰውን መውጫ መግቢያ አሳጥተው ሰላም የሚነፍጉ እኩዪች ናቸው። እነርሱ ከሚተነፍሱበት ሳንባ ብቻ የሚመነጨውን ትንፋሽ ሰው እንዲጋራ የሚፈልጉት ወያኔና የወያኔ አጨብጫቢዎች እውነትን አያውቋትም። የትግራይ ህዝብም የእነርሱ የመለመኛ ስልቻ ነው። አንድም ቀን አስበውለት አያውቁም። በስሙ ግን ያኔም ዛሬም ይነግዳሉ።
    ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ አለች አስቴር በዘፈኗ። የሶስት ጊዜ ወረራ ፈጽሞ መጨረሻ ላይ በመሪያቸው በአሜሪካ አሸማጋይነት ከሞት የተረፉት የወያኔ መሪዎች አሁንም ለትግራይ ህዝብና ለመላ ሃገሪቱ ስጋቶች ናቸው። ወያኔ ቀን እየሸመተ እንጂ ያለ ጦርነት ጭራሽ የማይኖር ቡድን ነው። የብልጽግናውን ብሄርተኛ አሁን ላይ ወያኔ በሾኬ የጠለፈውም ይመስላል። ጠ/ሚሩ ያልገባው ጉዳይ ወያኔ ማለት ጊንጥ መሆኑን ነው። ሰውነቱ ተከፍሎ ቀሪው የሚንቀሳቀስ። በፊትም ዛሬም ወደፊትም ላደረጉትና ለሚያደርጉት ክፋት ንስሃ የማይገቡ እርኩሞች ናቸው። መሬት ቆፍሮ ከአንገት በታች ቀብሮ የሚያሰቃይ አውሬ ቡድን ነው። ገና በፍራቻ የአርበኛ ልጆች ናቸው ተብለው በሽዋ፤ በጎንደር፤ በጎጃም በወሎና በሌሎቹ የሃገሪቱ ክፍሎች ተለቅመው የት እንደገቡ የማይታወቁ ስንቶች ናቸው? ቀጣፊው ወያኔ የትግራይ ሃይል ተባለ ሌላ ከመግደልና ከመዝረፍ ሌላ ሥልጠና የለውም። ሊኖረውም አይችልም። የነፍስ አባታቸው የሻቢያም ተንኮል ልክ እንደ ወያኔው ባህር ተሻጋሪ ሆኖ የሃገር የህዝብ ሃበሳ ላይበቃ ከእስራኤል እስከ ስካንድኔቪያን ሃገሮች፤ ከጀርመን እስከ አውስትራሊያ፤ ከጄኔቭ እስከ አሜሪካ አፍቃሪ ኢሳያስና ተጻራሪ ሃይሎች ሲፋለሙና የተጠለሉበትን ምድር ሰላም ሲያውኩና ንብረት ሲያወድሙ ለተመለከተ ሰው ችግራችን የጭንቅላት እንጂ የተወለድንበት ምድር እንዳለሆነ አብክሮ ይረዳል። ችግራችን አስተሳሰባዊ ነው። ሁሉን በቡጢና በውጊያ ብቻ ለመፍታት የምናረገው እብደት።
    ብቻ የዛሬውም ያለፈውን እየመሰለ፤ ሲልለትም ካለፈው በእጅጉ እየከፋ፤ ዛሬም ድሃ አደጎችና መከታ የሌላቸው ሰዎች የሚያነቡቧት የሃበሻዋ ምድር ብቻ ናት። ቀማኞችና ደም አፍሳሾች በወረፋ የሚራወጡባት ያቺ ምድር መቼ ይሆን ከጥይትና ከረሃብ ናዳ እፎይ የምትለው? ነው ዘርና ቋንቋችን እህል አርገን ወያኔ እንደ አፓርታይድ በቀየሰው ክልላችን ይህኑ ስናኝክ ህልፈተ ዓለም ይሆን? ጊዜ ያን ያሳየናል። እስከዚያው አብረን እናልቅስ!

Leave a Reply