የትግራይ ክልልን በመወከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ፌደሬሽን ምክር ቤት የህውሓት አባላት ሀላፊነታቸውን ለቀው እንዲወጡ አቶ ጌታቸው እረዳ ተናገሩ ============================================ አሻራ ሚዲያ መስከረም 25/2013 ዓ.ም ባህር ዳር *** ህወሓት በተለያዩ የፌደራል መንግሥት የፖለቲካ ሹመት ቦታ ላይ የነበሩ አባላቱን፣ የክልሉ ተወካይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ኃላፊነታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን አቶ ጌታቸው ረዳ ተናገሩ። አቶ ጌታቸው ረዳ የፓርላማው የስልጣን ዘመን በትናንትናው ዕለት ማክተሙን በመግለጽ፣ ከፓርላማው በተጨማሪ ፓርላማው ያቋቋመው መንግሥም፣ ካቢኔም የተመረጡት ለአምስት ዓመት መሆኑን ጠቅሰው የሰልጣን ዘመናቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልፀዋል። ስለዚህ ዛሬ በሚካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ የፓርላማ ዘመን 6ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ትግራይ ክልል ተወካዮቹን እንደማይሳተፉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። “ትግራይ ክልል ተወካዮች ከምክር ቤቱ እንዲወጡ ተነግሯቸዋል። በፓርላማ ብቻ ሳይሆን በካቢኔ ውስጥ፣ በሌሎች የመንግሥት የፖለቲካ ሹመት ቦታዎች ላይ የነበሩ የህወሓት ተወካዮች እንደዚሁ እንዲወጡ ተደርገዋል” ሲሉ ተናግረዋል። አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አምስተኛ የፓርላማ ዘመን ስድስተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ዛሬ ሰኞ መስከረም 25/2013 ዓ.ም 8:00 ሰዓት ይካሄዳል። ጉባኤው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚገኘው የስብስባ አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያው ሪፐብሊክ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሚያደርጉት ንግግር የሁለቱ ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ ይከፈታል።
Source: Link to the Post