የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽን እየጠበቅን ነው- የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን

በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት ታቅዶ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እስካሁን ምንም ዓይነት ስራ ካልጀመረበት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል።

ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርአያ የኮሚሽኑን ተደራሽነት ለማጠናከር ታስቦ የካቲት 4 ቀን 2016 በዋና ጽህፈት ቤቱ በተደረገው መድረክ እንዳስታወቁት ከትግራይ ጊዜያዊ አስትዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች ኃላፊዎች ጋር ከሁለት ወራት በፊት ተገናኝተው ነበር። 

በወቅቱም የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት “በአገራዊ ምክክሩ እንደሚያምኑበት እና አስፈላጊነቱን እንደሚቀበሉ” ማስታወቃቸውን ዋና ኮሚሽነሩ አስታወሰዋል። በክልሉ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መኖራቸው እና አስተዳደሩ ከሚያደርገው ጥልቅ ስብሰባ በኋላ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ለማሳወቅም ቀጠሮ ሰጥተው ነበር ተብሏል። 

አዲስ ማለዳ በተከታተለችው መድረክ ላይ መስፍን ዓርአያ እንደገልጹት “አሁን ረጅም ጊዜ የፈጀው ስብሰባው ተጠናቋል፤ በማንኛውም ጊዜ ጠርተውን ኮሚሽነሮች ሄደን እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ ተመሳሳይ ስራ እንጀምራለን ብለን ተስፋ አድርገናል” ብለዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ ማለዳ ለዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርአያ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሠራሽ ምክንያቶች እየተፈናቀሉ የሚገኙ ዜጎች በስራቸው ላይ ስለፈጠረው ጫና እንዲሁም በምን መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ስትል ጥያቄ አንስታለች። 

ዋና ኮሚሽነሩ እንዳሉት “ከግጭት እና ድርቅ/ረሃብ ጋር የተያያዙ ስራዎችን በዋናነት የሚሰሩ አካላት አሉ፤ የኛ ኃላፊነት አይደለም” አይደለም ብለዋል። ነገር ግን በየቦታው ተፈናቅለው የሚገኙ ዜጎች “ስራችን በየወረዳው የሚሰራ በመሆኑ በሚገኙበት ወረዳ ተሳታፊ ይሆናሉ። የተፈናቀሉበት ምክንያትም የአገራዊ ምክክሩ አካል ይደረጋል” ሲሉ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርአያ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።  

ላለፉት ሁለት ዓመታት ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም አካባቢዎች በርካታ ስራዎች በተለይም በኮሚሽኑ የሚሰሩ ስራዎችን መለየት፣ ተባባሪ አካላትን መምረጥ እንዲሁም የተሳታፊዎች ልየታ በመላ አገሪቱ በሚገኙ በ1 ሺህ 400 ወረዳዎች መስራት ተችሏል ተብሏል።

ኮሚሽኑ በዛሬው እለትም ከየካቲት 4 ቀን 2016 ጀምሮ የአገራዊ ምክክር ርዕሰ ጉዳዮች (አጀንዳ)ን የመቀበል ሥራ በይፋ መጀመሩን አስታውቋል። 

የርዕሰ ጉዳይ መሰብሰብ ሥራው በአገር ውስጥ በክልል እና በፌደራል ደረጃ የሚከናወን ሲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተደራሽ እንደሚሆኑበት ኮሚሽኑ የገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ በ8112 ነጻ የስልክ እና የአጭር ጽሁፍ መስመር፣ በኮሚሽኑ ድረ ገጽ እና በአካል ርዕሰ ጉዳዮችን ለኮሚሽኑ መስጠት እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ከዛሬ መርሃ ግብር ሰምታለች።

“በአገሪቱ ባለፉት ዓመታት ላለመግባባት እንዲሁም አለፍ ሲል ለጦርነት የዳረጉን ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚለውን ከህብረተሰቡ መቀበል ዋነኛ ስራችን ይሆናል” ሲሉም ዋና ኮሚሽነር መስፍን ገልጸዋል። የሚሰበሰቡ ርዕሰ ጉዳዮች እንደ አስፈላጊነታቸው ቅደም ተከትል ተሰጥቶ በአማካሪዎች የተዘጋጁ በኋላ ወደ አገር አቀፍ የምክክር ጉባዔ ሂደት ይሸጋገራሉ ተብሏል።

ጉባዔው ሲካሄድ እና ከተጠናቀቀ በኋላ የሚገኙ ምክረ ሐሳቦች ለህግ አውጪዎች፣ ለህግ አስፈጻሚዎች እና ለህግ ተርጓሚዎች እንዳስፈላጊነቱ ተልከው ወደ ተግባር እንዲቀየሩ ይደረጋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች በተግባር ላይ መዋላቸውን ማጣራት የመጨረሻ ተግባሩ ሲሆን ውጤቱንም ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ ማቋቋሚያ አዋጁ ይደነግጋል። 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ በፖለቲካም ሆነ በእምነት እና ሌሎች አስተሳሰቦች ወደአንድ ወገን ያደላ እንዳይሆን እና የተሳታፊዎች ምርጫም ወገንተኛ እንዳይሆን 65 የሚሆኑ በሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ሂደቱን እየተከታተሉ ይገኛሉ ተብሏል። 

በአገራዊ ምክክሩ “ማንንም ጥለን አንሄድም፤ ጫካ ያሉትን፣ ከተማ ሆነው የተቀየሙትንም ማንምም ሳይቀር ሁሉም አሸናፊ እንዲሆን እንጥራለን። ለታጣቂዎች አሁንም በእናንተ [መገናኛ ብዙኀን] በኩል ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉ ዋና ኮሚሽነሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ዋና ኮሚሽነር “ከጦርነት በኋላ ድርድር፤ ከድርድር በኋላ ምክክር አለ። ስለዚህ ከጦርነት በፊት ምክክር ይደረግ የእኛ ምክረ ሃሳብ ነው” ብለዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply