“የትጥቅ ትግል አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ራስ ምታት ሆኗል” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡ግንቦት 20 ከዛሬ 33 ዓመት በፊት በዛሬው ዕለት የወታደራዊ መንግስት ደርግ መውደቅን ተከትሎ…

“የትጥቅ ትግል አሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ራስ ምታት ሆኗል” ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ፡፡

ግንቦት 20 ከዛሬ 33 ዓመት በፊት በዛሬው ዕለት የወታደራዊ መንግስት ደርግ መውደቅን ተከትሎ ለተከታታይ 27 ዓመታት በደማቅ ሁኔታ ሲከበር መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ባለፉት 6 ዓመታት በዓሉን ካላንደር ይዝጋው እንጂ ከቀደሙት ግዚያት በደበዘዘ መልኩ እየታሰበ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው ደግሞ ከቀደሙት ግዜያት በተለየ መልኩ በበርካቶች ዘንድም ሲያወዛግብ ቆይቷል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ ይፋ የተደረገው እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገና ያልጸደቀው “የሕዝብ በዓላት እና የበዓላት አከባበር ረቂቅ አዋጅ” ተከብረው በሚውሉ ብሔራዊ ባላት ውስጥ ግንቦት 20ን አለማካተቱን ተመልክቶ ነው፡፡

ጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም የዛሬ 33 ዓመት እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ከሰላማዊ ትግሎች ይልቅ ትጥቅ ትግል ተመራጭ መሆኑ ምክንያቱ ምንድነው ሲል ፖለቲከኞችን ጠይቆበታል፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ የነበራቸው የእናት ፓርቲ እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮች በዚህ ዙሪያ ሃሳባቸውን ሰጥተውናል፡፡

በቅድሚያ የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሙላት ገመቹ ሀገራችን ዛሬ ላይ ድረስ ላለችበት ችግር አንዱ ይህ ትጥቅ ትግል መሆኑን አንስተው፡፡
በተለይም የስልጣን ተዋረዱ ከታች ወደላይ መሆን ሲገባው ከላይ ወደ ታች መሆኑ ችግሩን አብሶታል ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ሙላት ሁሉ የእናት ፓርቲው የህዝብ ግንኙነት እና ከፍተኛ አመራር አቶ ዳዊት ከበደ ትጥቅ ትግል እንደ ሀገር ተለማምደነዋል ሲሉ ይገልፁታል፡፡
ሰዎች ሀሳባቸውን በትጥቅ ትግል የሚያሳኩበትና ወደ መንግስት የሚመጡበትን እንደ ባህል የመቁጠር አባዜ ሊያበቃ ይገባል ብለዋል፡፡
የሀሳብ ትግል የመጫወቻ ሜዳዎች ሊመቻቹ ይገባል የሚሉት አቶ ዳዊት ይህን የማዛጋጀት የማመቻቸት ሀላፊነት ያለበት ደግሞ መንግስት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 33 ዓመታት ለውጥ ያላገኘው ይህ የትጥቅ ትግል ዛሬም በሀገራችን እንደ አንድ የፖለቲካዊ መፍትሄ ተደርጎ እየተወሰደ ይገኛል፡፡
እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉና ሌሎች ነፃና ገለልተኛ መሆን የሚገባቸው ተቋማት አሁንም ነፃና ገለልተኛ አለመሆናቸውና ጠንካራ ተቋማት አለመፈጠራቸው እንደ ምክንያትም ተነስቷል፡፡

ከጣብያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ሀገራችን ከዚህ አዙሪት መውጣት ካለባት ሁሉም አካል ሰላማዊ ትግል መምረጥ አለበት መንግስትም የሰላማዊ ትግል ሜዳውን ማመቻት ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአቤል ደጀኔ

ግንቦት 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply