
#የችሎት መረጃ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞችና ምሁራን በደሎች እየደረሱብን ነው አሉ! ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም… አሻራ ሚዲያ ፣ በአማራ ክልል ልዩ ሃይልን ለማፍረስ ከተደረገው እንቅስቃሴና ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት ከተጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረጉና በሶስት መዝገብ የተከሰሱ ጋዜጠኞች፣ ምሁራንና ፖለቲከኞች ዛሬ ግንቦት 16/2015 ዓ/ም የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበዋል፡፡ በዚህም በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ፣ በእነ ረ/ፕ ሲሳይ አውግቸውና ፣ጆን አሻግሬ የተባለ ወጣት ለብቻው በቀረበበት መዝገብ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የተከሰሱት ራሳቸው ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ፣ጋዜጠኛ ገነት አስማማውና ዶ/ር መሰረት ቀለመወርቅ ሲሆኑ በዛሬው ችሎት የቀረበው አቃቤ ህግም ለክስ መመስረቻ 15 ቀን ይሰጠኝ ሲል ጥያቄ ማቅረቡን ሮሃ ቲቪ በችሎት ተገኝታ ተከታትላለች፡፡ አቃቤ ህግ ፋይሉ የደረሰን ዛሬ ስለሆነ ለክስ መመስረቻ 15 ቀን ይሰጠኝ ቢልም የተከሳሽ ጠበቆች ግን የሽብር ወንጀሎችን ምርመራ ለመከላከል በወጣው ህግ መሰረት አቃቤ ህግ የሽብር ወንጀሎችን ምርመራ እንደሚመራ የተገለጸ ስለሆነና ይህንንም ምርመራ ከፖሊስ ጋር እየመራ ስለቀጠለ እንዳዲስ ፋይል ለመመርመሪያ 15 ቀን ሊጠይቅ እንደማይገባው በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ ጠበቆቹ አክለው ደንበኞቻቸው ከ41 _48 ቀን በእስር ላይ ስለቆዩ በዋስ ሊወጡ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩል በአንድ ሰው እስከ 65 ሰነድ ስላሰባሰብን ፣ እነዚህን እስክንመረምር የ15 ቀን ጊዜ ይሰጠን ብሏል፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግ “የተከሰሱበት ወንጀል ሞት ስላለበት በዋስ መውጣት የለባቸውም” ቢልም ጠበቆች ግን “ሞት የሚባለው ውንጀላ በደፈናው የቀረበና ፣ <እገሌ እገሌን ገደለ> የሚል ስለሌለበት በጅምላ እስረኞችን አስሮ ማቆየት ተገቢአይደለም” ሲሉ መከራከሪያቸውን አንስተዋል፡፡ በችሎቱ የተናገሩት ዶ/ር መሰረት “በተደጋጋሚ ግድያ ተፈጽሟል እየተባለ በችሎት የሚነሳው ሞራላችንን ለመንካት ነው እንጂ እኛ ይህን የሚያደርግ ስብዕና ኖረን የምንፈጽመው ተግባር አይደለም” ብለዋል፡፡ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው በበኩሏ “ እንደሌሎቹ ሁሉ በማንነቴ ከደረሰብኝ ጥቃት በተጨማሪም በሴትነቴ ላይ የደረሰብኝ ጾታዊ ትንኮሳ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ባቅርብም ፍ/ቤቱ ችላ ብሎ እያለፈብኝ ነው” ስትል አቤቱታዋን አቅርባለች፡፡ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋም “የአማራ ህዝብ የዘር ፍጅትና መፈናቀል በቃኝ ብሎ ሲወጣ ወደ ህዝብ የተኮሰው ራሱ ብልጽግና ነው ፣ እኛም የታሰርነው ይህን በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወማችን ነው” ብለዋል፡፡ችሎቱም ለአቃቤ ህግ የ15 ቀን የምርመራ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ሁለተኛው የችሎት መዝገብ የእነ ረዳት ፕ/ር ሲሳይ አውግቸው መዝገብ ሲሆን ረዳት ፕ/ር ሲሳይ አውግቸው ፣ ረ/ፕ ማዕረጉና አቶ ሄኖክን በተመለከተ አቃቤ ህግ የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ደርሶኛል ብሏል፡፡ በዚህም መዝገብም የ15 ቀን የምርመራ ጊዜ በመጠየቁ ጠበቆቹና አቃቤ ህግ ከእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ጋር ያደረግነው ክርክር ይያዝልን ሲሉ አልፈውታል፡፡ችሎቱም በተመሳሳይ የ15 ቀን የምርመራ ጊዜ ለአቃቤ ህግ ፈእቅዷል፡፡ ፖሊስ በዚህ በእነ ረዳት ፕ/ር ሲሳይ መዝገብ የነበሩትን ሰለሞን ልመንህና ንዋይ ዮሃንስ የተባሉትን ተከሳሾች በዋስ ቢለቀቁ ችግር የለብኝም በማለቱ በ10 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡ ሌላኛው በዚህ መዝገብ የተከሰሰውን ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን በተመለከተ አቃቤ ህግ 14 ቀን የጠየቀ ሲሆን ለዚህም “በሚዲያ ባደረገው ቅስቀሳ ሰዎች ሞተዋል፣ ይህን ለማጣራትም ወደ አማራ ክልል ቡድን ልከናል” የሚል ምክንያት አቅርቧል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው “ከእነ ረ/ፕ ሲሳይ ጋር የነበረ መዝገብ ነው ስለዚህ ምርመራው ተጠናቋል ፣ ለብቻው ተነጥሎ ማጣራት ሊደረግበት አይገባም” ብለዋል፡፡ ጋዜጠኛ ጎበዜ በበኩሉ በሚዲያ ባሰራጨሁት ነገር ከተከሰስኩ በሚዲያ ህጉ ነው መጠየቅ ያለብኝ ሲል ጠይቋል፡፡ በተጨማሪም “ ፖሊስ እኔን በሚመለከት ከድርጊቱ የማይቆጠብ የሚል ቃል በተደጋጋሚ ያነሳል ፤ ይህ ደግሞ እኔን ልማደኛ ወንጀለኛ ለማስመሰል ሆን ተብሎ የተደረገ ተግባር ነው፣ እኔ ግን በፍርድ ቤት ነጻ የተባልኩ ሰው ነኝ” ብሏል፡፡ግራ ቀኙን የተመለከተው ችሎቱም የ12 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ በሶስተኛው መዝገብ የተከሰሰው ጆን አሻግሬ የተባለው ወጣት ጉዳይን በሚመለከትም አቃቤ ህግና ጠበቆች ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ላይ የቀረበው ክርክር ይያዝልን ብለዋል፡፡ፍርድ ቤቱም በ50 ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ከእስር እንዲወጣ ወስኗል፡፡ ባጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ላይ የደረሰባቸውን በደል ፍርድ ቤቱ እንዲሰማቸው ጥረት ቢያደርጉም ዳኞቹ ጫና እንዳሳደሩባቸው ታዝበናል፡፡ ዘገባው የሮሃ ቲቪ ነው ። “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24
Source: Link to the Post