የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን “ጽንፈኛ ኃይሉ” በመሳሪያ መቶታል- የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን 

አማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ከትላንት እኩለ ቀን ጀምሮ ለተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል፤ ምክንያቱ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር “በጦር መሳሪያ ተመቶ” እንደሆነ አስታወቀ።

በትላንትናው ዕለት አብዛኛው የሰሜን ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል እንደተቋረጠበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስታወቁን አዲስ ማለዳ ዘግባ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ተቋሙ ከባህር ዳር – በደብረታቦር – ንፋስ መውጫ – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር “መበጠሱን” ብቻ ነበር ያስታወቀው። 

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ትላንት ምሽት “በወቅታዊ አሁናዊ ጉዳይ” በሰጠው መግለጫ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ “ጽንፈኛና ዘራፊ ኃይል” የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን በመሳሪያ እንደመቱት ገልጿል። 

ፖሊስ ኮሚሽኑ በመግለጫው “ህዝብን ከቀን ወደ ቀን ወደ ተወሳሰበ ችግር ለመክተት አልሞ እየሰራ ያለው ፅንፈኛ ዘራፊ ቡድኑ በለመደው መንገድ ዛሬ የካቲት 26/2016 ዓ/ም እኩለ ቀን አካባቢ ከባህር ዳር-ደብረታቦር-ንፋስ መውጫ-ጋሸና- አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በንፋስ መውጫ አካባቢ አንደኛው ፌዝ በመሳሪያ በመምታቱ ከሠዓት በኋላ ጀምሮ አብዛኛው የአማራ ክልል አካባቢ የመብራት አገልግሎት እንዲያጣ አድርጎታል” ሲል ታጣቂዎችን ወንጅሏል።

በትላንትናው ዕለት አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባገኘችው መረጃ ከባህር ዳር እስከ አላማጣ ከተዘረጋው መስመር በተጨማሪ ከደብረ ብርሃን-ሸዋሮቢት-ኮምቦልቻ የተዘረጋው መስመርም ሸዋ ሮቢት ከተማ አቅራቢያ “በመበጠሱ” ከሸዋ ሮቢትና ከሚሴ በስተቀር አብዛኛዎቹ የሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ መብራት የለም ተብሏል።

ከኮምቦልቻ በባቲ በኩል ኤሌክትሪክ ኃይል የሚደርሳቸው የአፋር ክልል መዲና ሠመራና የተለያዩ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም በወልዲያ አላማጣ መስመር ኃይል የሚያገኙት የትግራይ ክልል መዲና መቀሌን ጨምሮ አብዛኛዎቹ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው አዲስ ማለዳ ትላንት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘችው መረጃ ያሳያል። ይህ ዘገባ ዛሬ የካቲት 27 ቀን 2016 እስከወጣበት ድረስ አዲስ መረጃ አልወጣም። 

“የአማራን ህዝብ በማሠቃየትና ችግር ውስጥ በማስገባት ድል ይገኛል በሚል የእውር ድንበር የትግል ስልት የሚከተለው ፅንፈኛና ዘራፊ ኃይል ህዝቡን ወደ ተወሳሰበ ስቃይ አስገብቶታል” ያለው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን “መንግሰት ለአርሶ አደሩ የሚልከውን ማዳበሪያ እንዳይደርስ ጉዞውን እያያስተጓጎለና እየዘረፈ ስለመሆኑ ሁሉም የሚያውቀው የእለት ተዕለት ተግባሩ ሆኗል” ሲል ኮንኗል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን “በቀጣይም የህዝብን ስቃይና ምሬት የሚጨምሩ ተግባራትን በመፈፀም መንግስት እንዲህ አደረገ ለማለት በዝግጅት ላይ እንዳለም መረጃዎች ያሳያሉ” ያለ ሲሆን አዲስ ማለዳ በክልሉ የሚደረገውን የትጥቅ ትግል የሚደግፉ የብዙኀን መገናኛ ዲጂታል አማራጮች በተደጋጋሚ ታጣቂ ኃይሉ ከህዝብ ጋር ችግር እንደሌለበት፤ ይልቁንም “ለህዝቡ” እንደሚታገል ይገልጻሉ።

ስድስት ወራትን ባስቆጠረው በአማራ ክልል “ፋኖ” ተብለው የሚጠሩ ታጣቂዎች ከመንግስት ኃይል ጋር የገቡበት ፍልሚያ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም በኋላ መባባስ ታይቶበታል። ከተወሰኑ ቀናት በፊትም የማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት በስፍራው ለሚኖር “ከባድ ወታደራዊ ኦፕሬሽን” ሲባል ከአዲስ አበባ ደሴ/ ኮምቦልቻ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን እንዳስታወቀ አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም። 

የክልሉን የደህንነት ሁኔታ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ስርዓት መቆጣጠር አዳጋች ነው በሚል የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተቃውሞና ውዝግቦች ታጅቦም ቢሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለስድስት ወራት ካጸደቀ በኋላ በጥር ወር መጨረሻ ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞታል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply