የነዳጅ ድጎማውን በአግባቡ ለመተግበር 2 ሺህ ተቆጣጣሪዎች መሠማራታቸው ተገለፀ

አርብ ሀምሌ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራርን በተመለከተ ቁጥጥር የሚያደርጉ ኹለት ሺህ ተቆጣጣሪዎች መሠማራታቸውን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ዴሬሳ ኮቱ በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ ባለስልጣኑ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራርን የሚቆጣጠሩ ሰዎችን አሰልጥኗል።

ሰልጣኞቹም የነዳጅ ድጎማ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ከሆነበት ሰኔ 29 ቀን 2014 ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ቁጥጥር የማድረግ ሥራቸውን ጀምረዋል ብለዋል።

ከኹለት ሺህ ተቆጣጣሪዎች ውስጥ 70ዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ መሰማራቸውን የገለጹት ዴሬሳ፤ በመላ አገሪቷ በአጠቃላይ በዘጠኝ ክላስተር የተከፋፈሉ ተቆጣጣሪዎች በተለያዩ ከተማዋና ወረዳዎች ጭምር ተመድበው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በየአካባቢው የተመደቡ የነዳጅ ድጎማ አፈጻጸም ተቆጣጣሪዎች በየዕለቱ በነዳጅ ማደያዎች ያለውን ክምችት እንዲሁም የነዳጅ ሽያጭ በተመለከተ ቁጥጥር ያደርጋሉ።

በዋናነትም እያንዳንዱ ማደያ የደረሰውን ነዳጅ ጫኝ ቦቴ ተገቢውን ጭነት ይዞ መድረሱንና በአግባቡ ማራገፉን በተመለከተ ማረጋገጫ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።

በየአካባቢው የተሠማሩ ተቆጣጣሪዎች ከፌዴራል፣ ከክልልና ከተማ መስተዳድር ቢሮዎች እንዲሁም ከተለያዩ የትራንስፖርትና የነዳጅ ጉዳይ የሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ መሆናቸውን ዴሬሳ ጠቁመዋል።

ባለሙያዎቹም ከትራንስፖርትና ስምሪት ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱን ላይ የተደረገው የነዳጅ ድጎማው ለታለመለት አገልግሎት ውሏል ወይ የሚለውን እየተዘዋወሩ እንደሚቆጣጠሩም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈ የነዳጅ ድጎማው ዓላማ ታችኛውን ኢኮኖሚ ላይ የሚገኘውን ኅብረተሰብ ለመደገፍ በመሆኑ ድጎማውን የወሰዱ አሽከርካሪዎች በተተመነላቸው የትራንስፖርት ዋጋ ህብረተሰቡን እያገለገሉ ስለመሆኑ ባለሙያዎቹ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ችግር ሲገኝና የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ላልተፈለገ ሕገወጥ አገልግሎት ሲውልም ተቆጣጣሪዎች በየዕለቱ አስፈላጊውን ሪፖርት ያደርጋሉ። በሪፖርቱ መሠረት ችግር የተገኘባቸው ተሽከርካሪዎች ከነዳጅ ድጎማው ኮታ ይነሳሉ፤ አለፍ ሲልም ከትራንስፖርት አገልግሎት ስምሪት እንዲወጡ የሚያደርግ ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከጂቡቲ ተነስተው ማደያዎቻቸው ጋር መድረስ ከነበረባቸው 200 የነዳጅ ቦቴዎች መካከል 10ሩ ሆን ተብሎ የነዳጅ እጥረት እንዲፈጠር በማድረጋቸው መወረሳቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገልጿል። ቀሪዎቹ ቦቴዎች ላይ የተወሰደውን ርምጃ በተመለከተ ግን ለማጣራት ቢሞከርም ንግድ ቢሮውም ሆነ ባለስልጣኑ ዘንድ መልስ አልተገኘም።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፤ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ የተለያየ መጠን ያላቸውን ተሽከርካሪዎችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ከሰኔ 29 ቀን 2014 ጀምሮ ከ160 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ላይ ተግባራዊ ሆኗል።

በዚህም መሠረት ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) በቀን ሰባት ሊትር፣ መለስተኛ የከተማ ታክሲ (ላዳ) በቀን 25 ሊትር፣ ሚኒባስ ታክሲ በቀን 65 ሊትር፣ መለስተኛ አውቶቡስ በቀን 94 ሊትር፣ የከተማ አውቶብስ በቀን 102 ሊትር፣ አገር አቋራጭ አውቶቡስ በቀን 65 ሊትር ነዳጅ መቅዳት እንደሚችሉ ታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply