የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ተቃውሞ ቀረበበት

ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት የቀረበው አዲሱ የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፣ በሁለት የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል። በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቃውሞ የሰነዘሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ን ወክለው ምክር ቤት የገቡ አባላት ናቸው።
በምክር ቤቱ የኢዜማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አወቀ ሐምዛዬ በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “ምክር ቤቱ እያጸደቃቸው ያሉት የታክስ አዋጆች የደኸየውን እያደኸዩ የሚሄዱ ናቸው”  “ድሃው ላይ ነው እየጨመርን፤ ታክሶች እያጸደቅን ያለነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
“ድሃው በጣም እየጮኸ ነው” ያሉት ዶ/ር አወቀ ሐምዛዬ፤ “ታክስ ሲጣል፣ ተጠቃሚ ላይ ነው ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምናየው ሃብታሞች አይከፍሉም፤ ባለንብረቱ አይከፍልም። ድሆች ናቸው ታክስ  የሚከፍሉት” ሲሉ ተደራራቢ ታክስ ድሆች ላይ ጫናው እየበረታ መምጣቱን በመጠቆም ትችት ሰንዝረዋል።
ሌላው የአብን የምክር ቤት አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ “እኔ ይሄ የንብረት አዋጅ መጽደቅ ‘የለበትም’ ብዬ ነው የምከራከረው” ሲሉ ተቃሟቸውን አሰምተዋል። በማያያዝም፣ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህን የመክፈል አቅም የለውም። አሁን ባሉ ተደራራቢ ታክሶችና የማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ደረጃ፣ ኢትዮጵያውያን የንብረት ታክስን የሚከፍሉበት አቅም አላቸው ብዬ አላስብምና እንዲታይ ምክር ቤቱን መማጸን እፈልጋለሁ” ብለዋል።
“መኖሪያ ቤት የሚገነባው በሕይወት ዘመን አንዴ ነው” ያሉት ዶ/ር  ደሳለኝ፤ “በሕይወት ዘመኑ ሠርቶ ከሚያገኘው ንብረት ላይ መንግሥት እንዴት ታክስ ለመሰብሰብ ያስባል? አይከብድም ወይ?” ጥያቄ አቅርበዋል።
 አክለውም በሰጡት አስተያየት፤ “ይህ የአዋጁ አስፈላጊነት መርህ መሰራት ያለበት ከመኖሪያ ቤት ውጭ ያሉ ትርፍ የንግድ ህንፃዎች ላይ ነው” ብለዋል- ዶ/ር ደሳለኝ።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የንብረት ታክስ መጣልን አስፈላጊነት ሲያብራራ፤ “በከተሞች ውስጥ የሚፈራው ቋሚ ንብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከከተሞቹ ዕድገት ጋር እየጨመረ በመሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ የክልል መንግስታት ከዚህ ሃብት ተገቢውን ድርሻ በታክስ አማካኝነት እየሰበሰቡ አይደለም” ይላል።
የቋሚ ንብረት ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መሆኑን የሚያትተው ማብራሪያው፤ ለዚህ የቋሚ ንብረት ዋጋ መጨመር በክልልና በማዘጋጃ ቤት ደረጃ የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ይላል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በተደነገገው መሰረት፣ የንብረት ታክስ የሚጣልባቸው ንብረቶች፤ በከተማ ውስጥ የሚገኝ መሬት በመሬት ላይ የሚደረግ ማሻሻያና ህንፃ ናቸው።
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን በሦስት ተቃውሞና በአብላጫ የድጋፍ ድምጽ ለቋሚ ኮሚቴው መርቶታል።
የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት በ2015 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ባደረጉት የጋራ ስብሰባ፣ የንብረት ታክስ የመጣልና የመሰብሰብ ስልጣን የክልል መንግሥታት እንዲሆን መወሰናቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የንብረት ታክስን ማዕቀፍ የሚወስን አዋጅ ደግሞ የፌደራል መንግስት እንዲያወጣ መወሰናቸው ይታወቃል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply