የንጉስ ተክለሃይማኖት 122ኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም በደብረ ማርቆስ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተካሄደ! ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የንጉስ ተክለሃይማኖት 122ኛ ዓመት መታሰ…

የንጉስ ተክለሃይማኖት 122ኛ ዓመት መታሰቢያ ፕሮግራም በደብረ ማርቆስ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተካሄደ! ጥር 3 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ የንጉስ ተክለሃይማኖት 122ኛ ዓመት መታሰቢያ በመልዕክተ አድባር ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ግቢ ዛሬ የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማት አባቶችና የማህበረሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተከብሯል ። #የንጉሠ ጎጃም ወከፋ ንጉስ ተክለሃይማኖት 122ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ታስቧል ። ራስ አዳል ተሰማ /ንጉስ ተክለሃይማኖት/ የዘር ሃረጋቸዉ ከጎጃሙ ገዥ ዮሴዴቅ አቤዴቭ የሚመዘዝ ነዉ፡፡ ራስ አዳል ተሰማ በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግስት ጥር 13 ቀን 1873 ዓ.ም በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ‹‹ንጉሠ ከፋ ወጎጃም›› ተብሎ የሸዋው ንጉስ ምኒሊክ በተገኘበት ነገሠ (ተክለጻድቅ፣200፡59)፡፡“ንጉሥ ተክለ ሀይማት በጎጃምና በከፋ ነግሦ ከመጣ በኋላ በጎጃምና በዳሞት ሹም ሽር አደረገ፡፡ የበኩር ልጁን በዳሞት ራስ በዛብህ አሰኘ፤ ቀጥሎ ደግሞ በጎጃም በመንቆረር ታቦተ ማርቆስን ተክሎ ደበረ፡፡ ብዙ ቅፈፍ አግብቶ 318 ደብተራ ሰራለት፡፡ መልዕልተ አድባር (ከአድባራት በላይ) ይሁን አለ፡፡ ደብረ ማርቆስ ይባል እንጅ መንቆረር አይባል ብሎ አዋጅ ነገረ፡፡ አለቃ መልአከ ፀሐይ መሸሻን፣ ሊቀ ጠበብት ጽሐፌ ትዕዛዝ እሸቴን ሾመ፡፡ ለጥንት ባላአፈሮችም ለመንቆረርና ለዝና ልጆች የዣባጢን የጮቢ የሚባል ሀገር ምንጣፍ ተክቶ ሲሶ ግብዝና ለርሱ፣ ሁለት እጅ ለጥንት ባላአፈሮች ሰጠ፡፡” (የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 263) ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ራስ እያሉ ጀምሮ ከጎጃም የስልጣን ተቀናቃኞቻቸው ጋር እና ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር በርካታ ጦርነቶችን አካሂደዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሁለት ታላላቅ ዘመቻዎችን አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የሱዳን ደርቡሾች ድንበር ተሻግረው ጎንደር ድረስ በመግባት ጥር 10 ቀን 1880 ዓ/ም ቤተክርስቲያን አቃጥለው ቀሳውስቱንና ሲያርዷቸውና እንዲህ ተብሎ ሲገጠም፡- ተከተልኸኝ ብየ ዞሬ ዞሬ ሳይ፣ ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጎንደር ቀረህ ወይ? ወገራ አሳላፊ ደንቢያ እንጀራ ጣይ፣ ተበላህ ጎንደሬ አተትነሳም ወይ? በወቅቱ አጼ ዮሐንስ አስመራ ስለነበሩ ይህንን በቀል ንጉስ ተክለ ሀይማኖት እንዲበቀል መልክት በመላካቸው ንጉስ ተክለ ሀይማኖት 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) የሚሆን ሰራዊታቸውን ይዘው በመሄድ ድል አድርገዋል፡፡ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት በር በከፈተው ታላቁ የአድዋ ጦርነት ወቅትም የጎጃምን ጦር በመምራት 6000 (ስድስት ሺህ) ሰራዊት ይዘው በመዝመት ታላቅ ድል አስመዝግበዋል፡፡ የግዛት ዘመናቸውም ራስ አዳል ተሰማ ተብለው ከ1861-1872 ዓ/ም ንጉሥ ተክለ ሀይማኖት ተብለው ከ1873-1893 ዓ/ም በድምሩ ለ32 ዓመት ጎጃምን ገዝተዋል፡፡ በአጠቃላይ በዘመናቸው የተሻለ ነው ብለው ያሰቡትን ነገር ለሀገራቸው ጎጃም ሲፈፅሙ ኑረው ጥር 3 ቀን 1893 ዓ/ም በእለተ አርብ ደብረ ወርቅ ላይ አረፉ፡፡ለእኒህ የአገር ባለውለታ አፅማቸው ባረፈበት ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ መታሰቢያ የሚደረግላቸው ሲሆን በዚህ ዓመትም 122ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓላቸው ተከብሯል። መረጃው፦የ ደብረማርቆስ ኮሚኒኬሽን ነው:: “ውድ የአሻራ ሚዲያ ቤተሰቦች የአሻራ ሚዲያ ቻናልን ላይክና ሰብስክራይብ በማድረግ ድጋፋችሁን ታሳዩን ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።” ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- // Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw // Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 // ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply