የአሁኑ ትውልድ የአድዋን የአይበገሬነትና የድል አድራጊነት መንፈስ በመላበስ ሕዝባችንን ከተጋረጠበት ኹሉን አቀፍ የኅልውና አደጋ በመታደግ ታሪክ ለመስራት ሊነሳ እንደሚገባ የአብን የአዲስ አበ…

የአሁኑ ትውልድ የአድዋን የአይበገሬነትና የድል አድራጊነት መንፈስ በመላበስ ሕዝባችንን ከተጋረጠበት ኹሉን አቀፍ የኅልውና አደጋ በመታደግ ታሪክ ለመስራት ሊነሳ እንደሚገባ የአብን የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት 126ኛውን የአድዋ ድል በዓል የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም በራስ አምባ ሆቴል በፓናል ውይይት በድምቀት አክብሯል። አድዋ የዘመን ተሻጋሪ የፋኖነት ድልና አኩሪ ታሪክ ማሳያ በመሆኑ በዓሉን ስናከብር አድዋ ትውስታ ብቻ ሳይሆን በታሪክ አምድነቱ የአባቶቻችንን የአይበገሬነት፣ የድል አድራጊነት እንዲሁም የሕዝባችንን የሀገረ መንግስት ግንባታ አበርክቶት የምንዘክርበት ነው ያሉት የአብን የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ /ቤት ምክትል ሰብሳቢ እጩ ዶ/ር ይህአለም ታምሩ የዛሬው ትውልድ ሕዝባችን የተጋረጠበትን ኹሉን አቀፍ የኽልውና አደጋ በመቀልበስ የሕዝባችንን ደኅንነትና ተጠቃሚነት ለማስጠበቅ በጋራ ሊነሳ ይገባል ብለዋል ፡፡ እጩ ዶ/ር ይህአለም አክለውም ዛሬ 126ኛውን የአድዋ ድል በዓል ስናከብር ሕዝባችን በትሕነግና መሰሎቹ ወረራ ተፈጽሞበት ለአካላዊ ፣ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነልቦናዊ ድቀት ተዳርጎ በሁሉም አካባቢ ሕዝባችን እየተገደለና እየተሳደደ ይገኛል ብለዋል። በዚህ የታሪክ እጥፋት ላይ የምንገኝ የዚህ ትውልድ አባላት ታሪክን ከመጠበቅ ባለፈ ሕዝባችንን እየገጠመው ካለው ዘርፈ ብዙ አደጋ በመጠበቅ ታሪክ ለመስራት በጊዜ የለኝም መንፈስ ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል ። በዝግጅቱ ላይ “አድዋ! የነጠረ የትግል ጥበብ ለዘመን ተሻጋሪ ድል እና አኩሪ ታሪክ ” በተመለከተ የውይይት መነሻ ጽሁፍ በዶ/ር አለልኝ አስቻለ ቀርቧል። ዶ/ር አለልኝ በፅሁፋቸው እንደገፁት የአድዋ ድልና ቱርፋቶቹ ፣ አድዋና የታሪክ ተቃርኖ እንዲሁም ትውልዱ ከአድዋ ታሪክ ሊማር የሚገባቸው ነገሮችን በተመለከተ በፅሁፋቸው አቅርበዋል። በውይይት መነሻ ጽሁፉ አድዋ እናትና አባቶቻችን በጥበበኞቹ መሪዎቹ እምዬ ምኒሊክና እቴጌ ጠሐይቱ እየተመሩ ጭቆናና ግፍ ላይ ዘምተው ድል የተቀናጁበትና ነፃነትን ለትውልድ ያወረሱበት ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ በመሆኑ የዚህ ዘመን ትውልድም ሕዝባችን የገጠመውን የኅልውና አደጋ በመቀልበስ የአባቶቹ ልጆች መሆኑን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ተነስቷል። የአድዋ ድል በአማራ ፖለቲካ ላይ ያለው በጎ አስተዋፆ እንዲሁም ነፃነትንና ሉዓላዊነትን የማስከበር ፋይዳው የሚል የመነሻ ጽሑፍ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ /ቤት የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ በአቶ መላኩ አስፋው የቀረበ ሲሆን ፣ የአድዋ ድል ለአማራው ጀግንነቱን በተግባር ያሳየበት ድል መሆኑን የአሁኑ ትውልድ ሊገነዘበው ይገባል ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በጽሑፋቸውም እንደገለፁት አባቶቻችን የዓድዋ ድልን ያስገኙት ወቅቱን የመጠነ ዓለማአቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን በመረዳት የሚመጣውን አስቀድመው በመገመት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረጋቸው ነው። ይሁን እንጂ የዓድዋን ድል ያስገኘና አገርን ከውጭ ጠላት ጠብቆ ያቆየው የአማራ ሕዝብ በገዛ አገሩ የሚጨፈጨፍ ፣ የሚሳደድና የሚዋከብ ሕዝብ ሆኗል። የአማራ ሕዝብ ሁኔታ ወደ ሕዝባዊ ውርደት እንዲደርስ ጠላቶቹ አጥብቀው እየሰሩ ያሉ ሲሆን ይህን ሁኔታ ለመቀልበስ የአማራ ሕዝብ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል። በውይይቱ መጨረሻ ፣ በቀረበው የመነሻ ጽሁፍ ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል ሲል የአብን የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ /ቤት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ገልጧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply