
”የአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ፣ በእግዚአብሔርም በሕዝብም በታሪክም ፊት የሚያስመሰግንና ተጠቃሽ የሆነ መልካም ሥራ (አለዚያም ደግሞ [አያደድርገውና] የማይሽር ተወቃሽ ጠባሳ ታሪክ) የምትጽፉበት ወቅት ነው፡፡” (መምህር ያረጋል አበጋዝ እንደጻፉት) ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለመስጠት ያላትን ሁለንተናዊ ዐቅም በእጅጉ ሊያሳልጥ የሚችል ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከመቅረቡ በፊት ሚያዚያ መጨረሻ ላይ ቀርቦ ነበር፡፡ ይህ የስትራቴጂክ (መሪ ዕቅድ) ጥናት በዘርፉ አሉ በሚባሉ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብትና የስልታዊ ዐቅድ ባለሞያዎች እንዲሁም በቤ/ክ ሊቃውንት ብዙ ተደክሞበት የተሠራ ነው፡፡ ይህ የተዘጋጀው የመንፈሳዊ ልማት እና የማኅበራዊ ልማት ዕቅድ ይኸንኑ አገልግሎት በሥራ ላይ ለማዋል ከሚያስፈልገው የአደረጃጀት አወቃቀር ጋር የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ባሉበት ቀርቦ ነበር፡፡ ሆኖም እነዚህ ብፁዓን አባቶች የቀረበውን የመንፈሳዊና ማኅበራዊ ልማት ዕቅድ ቢያመሰግኑትም የሚተገበርበትን የመዋቅር (አሠራር) ጉዳይ ግን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ ዕቅድ የሚተገበርበት መንገድ ከሌለ ጥናት ብቻውን ምን ፋይዳ አለው? በዚህ ሁኔታ ጥናቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የመቅረብ ዕድሉ ሩቅ ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ ከዚሁም ጋር የቤተ ክርስቲያን ችግሮችን በየዘርፉ እያጠና ዘላቂ መፍትሔዎች ላይ እንዲሠራ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመውና በጣም ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ያለው ግብረ ኃይልም በአዎንታ እንደማይታይና ሥራዎቹ የሚተገበሩ የመሆን ዕድላቸው ሩቅ መሆኑን በግልጽ እየሰማን ነው፡፡ ከዚህ የተነሣም አሁን ባለው የቤተ ክህነት አስተዳደር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አሠራር በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የተነሣ ከገባበት የተወሳሰበ ችግር የመውጣትና ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት የሚፈጽም አካል የመሆን ዕድል እንደማይኖረው ቁርጡን አሳውቀዋል (አሁን ባለው መዋቅር እስካሁን ያልቆረጠላቸው ካሉ ለማለት ነው እንጂ ብዙዎቻችንስ ቁርጣችንን ካወቅን ዘመናት ተቆጥረዋል)፡፡ በዚሁ የዘላቂ መፍትሔ ግብረ ኃይል ሥር ባለ አንድ ክፍል በጥሩ ጥናት ተዘጋጅቶ የቀረበው የኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥ ሂደት ረቂቅ መመሪያንም በመልካም እንዳልተቀበሉት ተሰምቷል፡፡ በየዘርፉ ብዙ መሥራት የሚችሉ ልጆች እያሏት ግን ቤተ ክርስቲያኒቱ የእነርሱ ብቻ የግል ድርጅት በምትመስላቸው አካላት ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህን ሁሉ ከባድ ዋጋ እየከፈለች የምትቀጥለው እስከ መቼ ይሆን? አሁን የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደራዊ መዋቅር ያለበት ሁኔታ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በ1940ቹና 50ዎቹ የነበረችበትን የተመሰቃቀለ ሁኔታ የሚመስል ነው፡፡ በዚሁም ላይ በአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥ ሂደቱ የሚፈጸምበት መመሪያ አስቀድሞ ሳይጽድቅ ወደ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሚገባ ከሆነ፣ ቤተ ክርስቲያንን እጅግ በጣም ለከፋሰ አደጋ አሳልፈው መስጠታቸው ነው፡፡ በዚያውም ላይ ከሕገ ወጦቹ እናካትታለን የሚባል ከሆነ ደግሞ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ለማፍረስ በሚደረገው ክፉ ሥራ ላይ የስምምነት ፊርማ እንደ ማስቀመጥ ነው፡፡ በአጠቃላይ ያለው ሂደት መቃብሯን እንደ ሙሴ መቃብር መሰወር እንዳይሆን በእጅጉ ያስጨንቃል! ክርስቶስን ብቻ የተሸከማችሁና እርሱን ብቻ የምታስቀድሙ እውነተኛ ብፁዓን አባቶቻችን ሆይ፤ የአሁኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባዔ፣ በእግዚአብሔርም በሕዝብም በታሪክም ፊት የሚያስመሰግንና ተጠቃሽ የሆነ መልካም ሥራ (አለዚያም ደግሞ [አያደድርገውና] የማይሽር ተወቃሽ ጠባሳ ታሪክ) የምትጽፉበት ወቅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን እነ ቅዱስ አትናቴዎስን፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን፣ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘንጾኪያን፣ . . . በእጅጉ የምትፈልግበት ወቅት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ብፁዓን አባቶቻችን ሆይ፣ እኛ ልጆቻችሁ በዚህ ምልዐተ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በላይዋ ላይ ያንዣበቡባትን ከባባድ ፈተናዎች፣ በጌታ መቃብር ላይ አይሁድ ጭነዋቸው እንደ ነበሩት ድንጋዮች ገለባብጣችሁ የቤተ ክርስቲያን አሠራር ከገባበት ውስብስብ ችግር የሚወጣበትን ትንሣኤ ታሳዩናላችሁ ብለን እንጠብቃለን!
Source: Link to the Post