
“…የአማራ ህዝብ ታሪካዊ ግዛቶቹን ለህወሓት አሳልፎ ለመስጠት በኦሮሞ ብልጽግና በኩል የሚደረገው ሩጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት!…” የአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ)… ግንቦት 17/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ለአማራ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮች ከአማራ ሕዝባዊ ኮሚቴ የተሰጠ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ! አማራ-ጠሉ ስርዓት ከተገነባበት 1983 ዓ/ም ጀምሮ የአማራ ሕዝብ እያለፈበት ያለው እጅግ አሰቃቂ መከራ ከማንም ፊት የተሰወረ አይደለም። ይህ ውርደት እና አሰቃቂ መከራ የተፈጸመው የአማራ ክልልን ስሙን እየቀያየረ ሲመራ የኖረው፤ አሁን “የአማራ ብልጽግና” የሚል መጠሪያ ላይ የደረሰው የአማራ-ጠሉ ስርዓት አማራዊ በሆነው ተወካይ ቡድን ቀዳሚ አጋፋሪነት ነው። ይህ የገዛ ሕዝቡን አስሮ በማስገረፍ እና በመግረፍ የተሰማራ ቡድን አሁን ላይ ይህንን ስራውን በተለመደው መንገድ ማስኬድ ባለመቻሉ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገኛል። በመሆኑም በየሳምንቱ ስብሰባ ላይ ይቀመጣል። ከሕዝቡ ጋር ያጣላው የራሱ አሽከርነት አባዜ መሆኑን ረስቶ “ከሕዝቡ ጋር ያጣላኝ የጽንፈኞች ሴራ ነው” ሲል የራሱን ጭራ ወደ አማራ ሕዝብ እውነተኛ ልጆች እየወረወረ ይገኛል። የአማራ ሕዝብ ትግል በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ባህር ዳር መቀመጥ አስፈርቷችሁ አዲስ አበባ ላይ ለከረማችሁት ለእናንተ መዘርዘር አያስፈልገንም። ስለሆነም ይህንን የሕዝብ ቁጣ ወደ መልካም ምዕራፍ መቀየር ከፈለጋችሁ፤ ስብሰባ ያስቀመጣችሁ መፍትሄ የማምጣት ፍላጎት አድሮባችሁ ከሆነ ልታጤኗቸው የሚገቡ በርካታ ነጥቦች እንዳሉ ለማሳሰብ እንወዳለ። ይህን ማስጠንቀቂያ ለመጻፍ የወደድነውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የታችኛውና የመካከለኛው መዋቅሮች አማራ የአማራን ሕዝብ አሁን ያለበትን ከፍተኛ የውርደት ማጥ በመረዳት ለመፍትሄው በመስራት ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ስላሉን ነው። የእኛም ፍላጎት የአማራ ሕዝብ ችግር ለሚገባው ሁሉ እገዛ አድርጎ የህዝባችንን መከራ ማስቆም በመሆኑ ይህንን ማሳሰቢያ ለመጻፍ ወሰንን። የአማራ ብልጽግና አመራሮች አሁን የተቀመጣችሁት ስብሰባ ምናልባትም የመጨረሻ ስብሰባ ሊሆን እንደሚችል መጠቆም እንወዳለን። የመጨረሻ እድላችሁን እንደቀድሞ ከስብሰባ መልስ አዲስ አበባ ተጉዛችሁ ከኦሮሞ ብልጽግና መሪዎች ጋር ፎቶ ተነስታችሁ በመለጠፍ እንደማትቀልዱበት ተስፋ እናድርግና በዚህ ስብሰባችሁ ላይ ልታነሷቸው የሚገቡ ነጥቦችን እንጠቁማችሁ። 1. ፓርቲያችሁ “ሽብርተኛ” በሚል የቀልድ ክስ እስር ቤት ያጎራቸው የአማራ ህዝብ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች እና ምሁራኖች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ 2. እነዚህ እስረኞች ከተፈቱ በኋላ እነሱን የጨመረ፣ በሀገር ወስጥ እና በውጭም ሀገር የሚገኙ የአማራ ማህበራትን ያካተተ፣ የአማራ ብልጽግናም እንደ አንድ ተሳታፊ የሚካፈልበት (እንጂ የማይሰበርበት) አማራ-አቀፍ ምክክር በአስቸኳይ እንዲደረግ፣ 3. የኦሮሞ ብልጽግና በኦሮሚያ የሚያደርሰውን የአማራ ህዝብ እልቂት በተመለከተ ሲጠየቅ የሚያሳብብበት “ኦነግ ሸኔ” የተባለው ገዳይ ቡድን ከዚህ በኋላ በኦሮሚያ ክልል ከነትጥቁ እየተዘዋወረ የአማራን ህዝብ የሚጨርስበትን ሁኔታ ለማስቆም በቀና ሁኔታ ምን እንዳሰበ በአስቸኳይ ለአማራ ህዝብ ግልጽ እንዲያደርግ፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም ይህ “ሸኔ” እየተባለ የሚጠራው ቡድን በአማራ ህዝብ ላይ አሰቃቂ የጅምላ ፍጅት በሚያደርግበት ሶስት አመታት ውስጥ የኦሮሞ ብልጽግና የሀገር መከላከያ ሰራዊትን እርዳታ ጠይቆ፤ የራሱን በ37 ዙር የሰለጠነ በርካታ ቁጥር ያለው ልዩ ኃይል አሰማርቶ የአማራን ህዝብ እልቂት ሊያስቆም ያልቻለበትን ምክንያት ለአማራ ህዝብ ግልጽ እንዲያደርግ። 4. በሌላ በኩል በኦሮሞ ብልጽግና የሚዘወረው የፌደራል መንግስት ለሶስት አመታት የአማራ ህዝብ የእልቂት መድረክ በሆነው የኦሮሚያ ክልል የሀገር መከላከያ ሰራዊትን አዘምቶ የንጹሀንን ህይወት ለመታደግ ሳይሞክር በአሁን ወቅት ምንም አይነት የጸጥታ ችግር በሌለበት የአማራ ክልል የኦሮሞ ጄነራሎች የሚመሩትን የመከላከያ ሰራዊት አሰማርቶ የአማራን ህዝብ ፤ እያዋከበ፣ ተኩሶ እየገደለ፣እያሸበረ ያለበትን ምክንያት ግልጽ እንዲያደርግ። 5. የአማራ ህዝብ በማንነቱ ምክንያት ብቻ በኦሮሚያ ክልል የሚደርስበትን የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ዘር ማጽዳትና ማፈናቀል በተመለከተ ሌሎች የብልጽግና ፓርቲ አባላት ማለትም የሱማሌ፣ የአፋር፣የደቡብ ህዝቦች፣ የሲዳማ፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የሀረሬ ብልጽግና ፓርቲዎች ያላቸውን አቋም ግልጽ እንዲያደርጉ። እነዚህ ፓርቲዎች የአማራ ህዝብ ይህንን ሁሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲያስተናግድ ምንም አይነት ድምጽ በራሳቸው ሊያሰሙ አልቻሉም። ማንም ግለሰብ (ወይም ድርጅት) በዘር ማጥፋት እና ማጽዳት ፊት ገለልተኛ አቋም ሊይዝ ስለማይችል አቋማቸውን ግልጽ እንዲያደርጉ። 6. የኦሮሞ ብልጽግና በግልጽ ዘረኝነት ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን በተለይ አማሮችን ቤታቸውን በማፍረስ “ሸገር ከተማ” የተባለውን ፕሮጀክት ለማሰሪያ ሌት ተቀን ሳይል እየሰራ ይገኛል። በዚህም ግልጽ የዘረኝነት ፖሊሲ እና እርምጃው “ህገወጥ” ሲል የሚያፈርሰው ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን ቤት በተለይ ደግሞ የአማራ ተወላጅ የሆኑትን ነው። በዚህ የዘር ማጽዳት ፕሮጀክት ውስጥ ያደረጋቸው በርካታ ወንጀሎችን የሚያጣራ ግብረኃይል እንዲቋቋም። በዛ ላይ ህገወጥ የሚላቸው ቤቶች አብዛኞቹ ካርታ እና ፕላን የወጣላቸው መንገድ ዳር ላይ የተሰሩትን ቤቶች ጭምር መሆናቸውን በማሳሰብ ለዚህ የዘረኝነት ድርጊቱ ተጠያቂነት እንዲኖረው። 7. ከወለጋ እና ሌሎች የኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም “የሸገር ከተማ” ከተባሉ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በዘረኛው የኦሮሚያው ብልጽግና ፖሊሲ ተፈናቅለው በደብረብርሀን፣በደሴ፣ በባህርዳር የሚገኙ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ ወደ መደበኛ የሰው ልጅ ኑሮ የሚመለሱበትን ሁኔታ የኦሮሞ ብልጽግና እና ሌሎች የክልል ፓርቲዎች እንዲመክሩበት፣ ለነገ የማይባል ስራ መሰራት እንዳለበት። በተረፈ ይህ ሁሉ የአማራ ተወላጆች ለሶስት አመታት በመጠለያ ጣቢያዎች በታጎሩበት ሁኔታ የአማራን ህዝብ ወክያለሁ ብሎ ማውራት ለአማራ ብልጽግናዎች ከሞት የባሰ ውርደት እንደሆነ እንዲታወቅ። የአማራ ህዝብ ከአምራች ህዝብነት ወደ ተመጽዋች ተፈናቃይነት ወርዶ የጨለማ ህይወት በሚገፋበት ሁኔታ ምንም እንዳልተፈጠረ የአማራ ክልልን እንመራለን ማለት እንደማይቻል ለአማራ ክልል ብልጽግናዎች ለማስታወስ እንወዳለን። 8. ኦሮሞ ብልጽግና መራሹ የፌደራል መንግስት በአማራ ክልል ላይ ለሚያደርጋቸው ኢ-ህገመንግስታዊ የእብሪት እርምጃዎች ለምሳሌ ያለ ክልሉ እውቅና የመከላከያ ሰራዊትን አሰማርቶ ህዝብን መግደል፣ የአማራ መብት ተሟጋቾችን ጭምር እየደበደበ ማሰር የሌሎችን ክልል ልዩ ኃይሎች ከእነ ትጥቃቸው ባሉበት ሁኔታ የአማራ ልዩ ኃይልን እያሳደደ እና ማስፈራራት የመሳሰሉ የአማራ ክልልን ህገመንግስታዊ ሉአላዊነት ከማስጠበቅ አንጻር እና የክልሉን መንግስት ያለውን እጅግ ልፍስፍስ አቋም መገምገም። 9. የአማራ ክልል ለብዝሃነት ካለው በጎ ምልከታ አንጻር ከክልሉ ምክር ቤት ይሁንታ የተፈጠረው የከሚሴ ልዩ የብሄረሰብ ዞን ለኦነግ ሽኔ ዋሻ በመሆን እያገለገለ የሰሜን ሸዋ ከተሞች በተደጋጋሚ የሚጠቁበት፤ በተለይ የአጣዬ ከተማ ለዘጠኝ ጊዜ የወደመበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
Source: Link to the Post