
የአማራ ልዩ ኃይል መፍረስን በተመለከተ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ! ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አሥፈፃሚ ኮሚቴ በ27/07/2015 ዓ.ም. ስብሰባ በማድረግ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በመርህ ደረጃ የክልል ልዩ ኃይል መፍረስ እንዳለበት እና ሀገራዊ በሆነ ተክለ ሰውነት በተላበሰ የመከላከያ ሠራዊት መጠናከር እንዳለበት ፓርቲያችን የሚያምንበት ጉዳይ ቢሆንም ከወቅታዊ ሁኔታዎች አንፃር እና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ጉዳዩ ተቀባይነት የለውም፡፡ የአማራ ልዩ ኃይል በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ዙር ጦርነቶች የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይልን ታድጎ የኦህዴድ/ብልፅግናን በትረ-ስልጣን ካጸናለት በኋላ —የአማራ ልዩ ኃይል ከወልቃይትና ከራያ ይውጣ፤ የእኛ ዓላማ ህግ ማስከበር እንጅ ‘ርስት ማስመለስ አይደ…ለም፤” በማለት በልዩ ኃይሉ፣ በፋኖው እና በሚኒሻው ደም ሲሳለቅ መስማት የተለመደ የዜና እወጃ ነበር፡፡ በማይካድራ፣ በጭና እና በተለያዩ የአማራ እና የአፋር ህዝብ ላይ ወያኔ ያደረገው እልቂት እና ውድመት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል እንዲፈርስ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ላይ በእኩል ደረጃና መጠን ተፈፃሚ በማይሆንበት ሁኔታ የአማራን ህዝብ ለጥቃት የሚዳርግ እኩይ ውሳኔ ስለሆነ ውሳኔውን ባልደራስ አጥብቆ ያወግዘዋል፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ በአንድ ብሄር የበላይነት በተዋቀረበት ሁኔታ፣ የኦሮሚያ ክልልዊ መንግሥት የልዩ ኃይል ምልምላ እያካሄደ ባለበት ወቅት እና ትጥቁንም በማይፈታበት ሁኔታ የአማራን ልዩ ኃይል እንዲፈታ ማድረግ በኦሮሚያ ክልል ጭፍጨፋ ለመፈፀም የሚኖራቸውን ዓላማ የሚያሳብቅ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዳልፈታ እየታወቀ እና አመራሮች ከሰላም ስምምነቱም በኋላ በአማራ ህዝብ ላይ እየገለፁ ያሉትን የጥላቻ ቅስቀሳ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብሎም የአማራ ርስቶችን ወልቃይት እና ራያን በኃይል ለማስመለስ እንዲረዳቸው የታሰበ የፖለቲካ ሴራ ስለሆነ ባልደራስ አጥብቆ ይቃወማል፡፡ በዚህ መሠረት፤ ➢የታረዱት ዜጎቻችን ደም ሳይደርቅ ኦነጋዊ -ብልጽግና ለዳግም እልቂት የአማራን እና የአፋርን ህዝብ እያመቻቸው ስለሆነ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚኒሻው ትጥቁን እንዳይፈታ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ➢ወልቃይት የሰው ልጅ የስቃይ፣ የጎሰኝነትና የዘር ማጽዳት ላለፉት አርባ ዓመታት አስተናግዳ ዛሬም ለሌላ እልቂት ተዘጋጅ እየተባለች እንቢልታ እየተነፋላት ስለሆነ እና ውሳኔው የአካባቢውን ማህበረሰብ ለጥቃት ቀጥተኛ ተጋላጭ የሚያደርግ አደገኛ ውሳኔ ስለሆነ የአማራ ህዝብ ከልዩ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ ➢ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፣ ምሁራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ ይህንን እኩይ ተግባር በመቃወም ከልዩ ኃይሉ ጎን እንድትቆሙ እና ገዢው ፓርቲ የወሰነውን ውሳኔ አጥብቃችሁ እንድትቃወሙ እንጠይቃለን፡፡ ➢የአማራ ክልል መንግሥት ይህን የአማራ ህዝብን ለአደጋ አጋላጭ የሚያደርግ ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔ እንዲቃወምና ተግባራዊ እንዳያደረግ በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ባልደራስ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ ባልደራስ ለእዉነተኛ ዲሞክራሲ ፓረቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አዲስ አበባ፣ኢትዮጵያ መጋቢት 28/2015 ዓ.ም
Source: Link to the Post