የአማራ ሕዝባዊ ኃይል/ፋኖ ትግሉ የአማራ ህዝብ ነጻነት እና የኢትዮጲያውያን እኩልነት እውን ሆኖ ማየት መሆኑን አርበኛ ዘመነ ካሴ ገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 6 ቀን 2014…

የአማራ ሕዝባዊ ኃይል/ፋኖ ትግሉ የአማራ ህዝብ ነጻነት እና የኢትዮጲያውያን እኩልነት እውን ሆኖ ማየት መሆኑን አርበኛ ዘመነ ካሴ ገለጸ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 6 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ህዝባዊ ኃይል/ፋኖ መሪ አርበኛ ዘመነ ካሴ ባስተላለፈው መልዕክት ትግላቸው የቁስ እርካታ ሳይሆን የነጻነትና የእኩልነት መሆኑን አስታውቋል። “ለሚመለከተው ሁሉ” በሚል ባስተላለፈው መልዕክት የአማራ ሕዝባዊ ኃይሉ/የፋኖ አባላት ወደ ወሎ የዘመቱት የቁስ ሰቀቀናቸውን ለማርካት ብለው ሳይሆን ለጠላት ሰቀቀን ለመሆን እንደሆነም ተገልጧል። “የኛ ሰቀቀን የአማራ ህዝብ ነጻነት፣ የኢትዮጲያውያን እኩልነት ነው። ደግሞም አድርገነዋል።” ሲልም በመልዕክቱ አስፍሯል። ለዚህም” የመርከብ ተራራ ሰንሰለቶች ይናገሩ ፥የአቃስታ ፥ጊምባና ቱሉ አውሊያ አድባራት ይመስክሩ ጠላትን አናቱን ቀጥቅጠን ሙትና ቁስለኛውን በሲኖ ትራክ አስጭነነዋል።” በሚል ተገልጧል። አርበኛ ዘመነ ሲቀጥል”ሁለት ሳምንት ወሎ ግንባር ቆይቻለሁ፥ አንድ ቢጫ ጀሪካን ከጋራጅ ተውሼ በግማሽ ሰአት ውስጥ ከምስጋና ጋር መመለሴን አስታውሳለሁ። ሰባራ መርፌ እንኳን አልነካንም።” ሲል የታጋዮች አላማ ለወገን ታማኝነት ስለመሆኑ አመልክቷል። “ለምንወደው ስልጡን ህዝብ መከታ ልንሆን ዘምተናል፥ ጠላቱንም አይኑ እያዬ ተበቅለንለታል፥ ከፍ ያለ ኩራትም ይሰማናል።” ሲል በመልዕክቱ ያሰፈረው አርበኛ ዘመነ የአማራውን መደራጀት እና አንድነት የማይፈልጉ የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ጠላቶች ዛሬም ባንድ ላይ እየጮሁ ስለመሆናቸውም ጠቁሟል። “ወሎ አማራ መሬት ላይ በተአምር ማር ብናዘንብ እንኳን እነዚህ ሃይሎች አሲድ አዘነቡ እንደሚሉን ቀድመን እናውቅ ስለነበር ጫጫታቸው አላስገረመንም።” ሲልም በመልዕክቱ አስፍሯል። “ይልቁንስ ጠላት ሲጮህ ስራችን በሚገባ እየከወንን መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፥ጮክ ብሎ ይነግረናል።” መልዕክቱን አስተላልፏል_አርበኛ ዘመነ ካሴ። በተረፈ ሰባራ ቅል እንኳን በጉያው ደብቆ መርጡ ለማርያም የደረሰ አንድ እንኳን አባል ቢገኝ እጣው መራራ እንደሚሆን ያስታወቀው አርበኛ ዘመነ “ትግላችን ይቀጥላል፤ ከፋፋይነትና ሴረኛነት ጉሮሮው ይታነቃል” ሲልም አክሏል። በመጨረሻም “እና መሰሪ ሃይሎች ሆይ ህዝቡን ተውት አይደናገር፥እኛ እንደሁ እንኳን በውሻ ጩኸት በአንበሳ ግሳትም አንደነብር” የሚል መልዕክቱንም አስተላልፏል። አሚማም ለሚመለከተው ሁሉ በሚል የተጻፈው መልዕክት የአርበኛ ዘመነ ካሴ መሆኑን አረጋግጧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply