የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት «እኔም ከተገፉት ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ!» በሚል በመተከል ተፈናቅለው ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ ላሉ አማራዎች የሚውል የገን…

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት «እኔም ከተገፉት ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ!» በሚል በመተከል ተፈናቅለው ለከፍተኛ ጉዳት እየተዳረጉ ላሉ አማራዎች የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ መርኃ ግብሩን በዛሬው እለት መጀመሩን አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ህዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት «እኔም ከተገፉት ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ!» በሚል ከተለያዩ የመተከል ወረዳዎች ለተፈናቀሉ አማራዎች የሚውል የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ መርኃ ግብሩን በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫና ማብራሪያ ሰጥቷል። መግለጫው የተሰጠው በእለተ ማክሰኞ ኅዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ላይ ቤሌር ኳስ ሜዳ ፊት ለፊት በሚገኘው የአብን ዋና ጽ/ቤት ነው። «እኔም ከተገፉት ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ!» የሚለው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማሰባሰብ መርሀ ግብር በዋናነት ከተለያዩ የመተከል አካባቢዎች ለተፈናቀሉ አማራዎች የሚውል መሆኑን ተገልጧል። የአብን የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ማሞ መግለጫውን ለጋዜጠኞች አንብበዋል። አሸባሪው ትሕነግ በአማራ ህዝብ ላይ እና በመከካከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው ዘግናኝ ጭፍጨፋን ያወገዘው የአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተሰማውን ሀዘንም ገልጧል። በአሸባሪው ትሕነግ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲሉ በግዳጅ ላይ እያሉ ለተሰው የፀጥታ አካላትና አሁን ላይም ህግ በማስከበር ላይ ለሚገኙ አካላት በሙሉ ላቅ ያለ ክብር እንዳለው በመግለፅ ምስጋናውን አቅርቧል። ዘርን መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች በበርካታ አካባቢዎች በሚኖሩ አማራዎች ላይ እየተፈፀመ መሆኑን የገለፁት አቶ ስንታየሁ በተለይም መተከል ላይ የአማራ ህዝብ ከመቸውም ጊዜ በላይ ለከፋ ሁለንተናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተዳረገ መሆኑን አስታውቀዋል። መንግስት በትሕነግ ላይ እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃ አጠናክሮ በመቀጠል በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት ሊያረጋግጥ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በመተከል የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአማራ ላይ እየፈፀሙት ያለውን ተደጋጋሚ ግድያና ማፈናቀል ያወገዘው የአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት መንግስት ቀድሞ በመከላከል ረገድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እንዲሁም የሲቪክ ድርጅቶችና መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በድጋፉ የድርሻቸውን እንዲወጡ ሲል ጠይቋል። ከተፈፀመው ጭፍጨፋ ባሻገር አሁን ላይ በመተከል የተለያዩ ወረዳዎች በሽህዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ተፈናቅለው አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ በእጅጉ የሚሹበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የገለፀው ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ይህን አሳሰቢ ችግር ታሳቢ በማድረግ ነው «እኔም ከተገፉት ወገኖቼ ጎን እቆማለሁ!» የሚል የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብር ያዘጋጀሁት ብሏል። መላው የአዲስ አበባ ህዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው ጽ/ቤቱ ጥሪ ያቀረበው። ድጋፍ የመስጠት መርኃ ግብሩም እስከ ታህሳስ 4 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን ቀበና ቤልኤር ኳስ ሜዳው ፊት ለፊት ወደ ሚኒልክ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ የአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ድረስ በመገኘት እንድትደግፉ ሲል ጥሪ አድርጓል። ድጋፉንም በአቢሲኒያ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 46711734 ወይም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000359362793 ከአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ገቢ ማድረግ የምትችሉ መሆኑን ተጠቁሟል። በመድረኩ የተገኙት የአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ም/ሊቀመንበር አቶ ይኸአለም ታምሩም ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ይኸአለም ሲቀጥሉ የተፈናቀሉ አማራዎችን ለመደገፍም ሆነ ከጥቃት ለመከላከል በመንግስት በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም የተጠናከረ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል እንዲሁም ተፈናቃዮች በዘላቂነት የሚቋቋሙበትንና ወንጀለኞችም በህግ ጥላ ስር የሚውሉበት መንገድ እንዲፈለግ ሲሉ ነው የአማራ ክልል፣የቤንሻንጉል ጉምዝና የፌደራል መንግስትን ያሳሰቡት። አቶ ይኸአለም ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነውና በመተከል ቤተሰባቸውን ተነጥቀው በከፋ ችግር ላይ ለወደቁ ወገኖቻችን እንድረስላቸው ሲል የአብን አዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ላደረገው የድጋፍ ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ እንድትሰጡ እንጠይቃለን ብለዋል። ሙሉ መረጃውን በአማራ ሚዲያ ማዕከል የዩቱብ አድራሻ የምናጋራ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply