የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ትንኮሳ መጀመሩን ገለጸ፡፡የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከሰሞኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስ…

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ትንኮሳ መጀመሩን ገለጸ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከሰሞኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ ምላሽ ሰጥቷል። ሙሉ መግለጫዉ እንደሚከተለው ቀርቧል…

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም የአማራ ክልል ተማሪዎች መማሪያ መጻህፍትን እንደሰበብ ተመርኩዞ ያወጣውን የዛቻ እና የጠብ አጫሪነት መግለጫ ተመልክተናል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአማራ ክልል የትምህርት ሥርዓትን በማጣቀስ የተሳሳተ ካርታ ተሰርቷል ሲል ያወጣው መግለጫ በተሳሳተ ካርታ ወደ አማራ ክልል ተካተዋል ያላቸውን አካባቢ ሕዝቦች ታሪካዊ እውነታን፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ፣ አሳሳች እና የጠብ አጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ መግለጫ በመሆኑ እና በትናንትናው እለት ማለትም መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ከነበረበት አካባቢ በመንቀሳቀስ የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ ነዋሪዎችን በመግደል እና በማሰቃየት ላይ ይገኛል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአማራ ክልል የተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍ ውስጥ የተሳሳተ ካርታ ተሰርቷል ሲል ባወጣው መግለጫ ሊያመላክታቸው የተፈለጉት አካባቢዎች ካለፉት 30 ዓመታት በፊት ጀምሮ የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያሉባቸው ወረዳዎች የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን ሲያቀርቡባቸው በነበሩ ቦታዎች ላይ መኾኑ ግልጽ ነው፡፡

አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ከመጽደቁ በፊት በተስተዋሉት የአስተዳደራዊ መዋቅሮች እና አደረጃጀት ቅመራ ጅማሬ አንስቶ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመፈጸሙ ምክንያት ጦርነት እስከተቀሰቀሰበት ግዜ ድረስ የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች በወቅቱ ለነበረው መንግስት የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን በማንሳት መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲጠይቁ የነበሩ መሆኑን በበርካታ ታሪካዊ ሁነቶችና ተጨባጭ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲጠይቁ የነበሩ ሕዝቦች እና አካባቢዎችን ለበርካታ ዘመናት በኃይል ሲገዛ የነበው የቀድሞው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች ላነሱት ታሪካዊና ሕጋዊ ጥያቄዎች ሕጋዊ አሰራርን የተከተለ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የአካባበው ተወላጆችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ አስተባባሪዎችን በማሰር፣ በማሰደድ እና በመግደል የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ እስከ ሰሜኑ የህግ ማስከበር ጊዜ ድረስ እንዲገፋ አድርጎታል ብሏል።

የማንነት እና የአስተዳደር መብት ዙሪያ ላነሳቸው ጥቄዎች የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች ትግል በተፋፋመበትና ከፍተኛ መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ በሚገኝበት ወቅት ህወሓት የሠሜን ዕዝ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን አሰቃቂ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሁሉንም ኢትዮጵያዊያንን በማቀናጀት ለሁለት ዓመታት የቆየ የሕግ ማስከበር እርምጃ ለመውሰድ የተገደደበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወሳል፡፡

የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎቹ ለዘመናት የታፈኑበት ሕዝብም ከማዕከላዊው መንግስት ጎን ተሰልፎ በህ.ወ.ሓ.ት የክህደት ተግባር በኢትዮጵያ ሕልውና እና ሉአላዊነትት ላይ የተጋረጠውን ግልጽ አደጋ እንዲቀለበስ የበኩሉን አስተዋጽዖ ከማበርከቱ ባሻገር በሂደቱ ህወሓት በኃይል ተገፍፎባቸው የነበረውን የማንነትና ጥያቄና ራስን በራስ የማስተዳደር ነጻነት የተቀዳጁበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በዚህም ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች ህዝብ እንደማንኛውም የሀገሪቱ ሕዝብ ሁሉ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚነት መብቱ ሊቀለበስ የማይችል በመሆኑ በቀድሞው የህ.ወ.ኃ.ት እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት መካከል የፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ጀምሮ የአማራ ክልል እንደሌሎቹ ዞኖችና የልማት ትሩፋቶች ሁሉ የአካባቢው ሕዝብም በትምህርቱም መስክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡

አካባቢዎቹን በተመለከተ የነበረው፣ ያለው እና የሚኖረው እውነታ ይሄ ሆኖ ሳለ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ/ም ከፕሪቶሪያው ስምምነት ከመፈረሙ በፊት በስራ ላይ የዋሉ የአማራ ክልል ተማሪዎች እንደሌሎቹ አካባቢዎች የነዚህ አካባቢ ህፃናትም የመማራ መብታቸው እንዲከበር የአማራ ክልል መንግስት ግዴታውን መወጣቱን ሰበብ በማድረግ በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ የጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣቱ ካለፉት ድርብርብ ውድቀቶች ትምህርት አለመውሰድን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

የተፈጠሩ ችግሮችን በህግ አግባብ እንዲፈታ እተደረገ ያለውን ጥረት የአማራ ክልል መንግስት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ባለበት ሁኔታ በህዝብ መጎሳቆልና በወጣቶች እልቂት ትምህርት አለመወሰዱና የተለመደ ትንኮሳ በማድረግ ላይ መሆኑ እጅጉን አሳዝኖናል፡፡

ስለሆነም የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብ፣ ሀገራችንንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት በመቆጠብ ከለመደው አጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣና የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንዲሁም አንድ ሀገር ለመገንባት ለሚፈለገው ዘላቂ ሠላም እና ለሕዝቦች አንድነት መጽናት በሚበጅ ሐሳብና ተግባር ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን ሲል መግለጫውን አጠናቅቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply