“የአማራ ታጣቂዎች” ያቋቋሟቸውን አስተዳደሮች ለማፍረስ ከፌደራል መንግስት ጋር ተስማምተናል ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ

በምዕራብ ትግራይ በፀለምቲ አካባቢ እና በደቡብ ትግራይ አንዳንድ አካባቢዎች በአማራ ታጣቂዎች የተቋቋሙትን አስተዳደሮች ለማፍረስ የፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ሲሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ኃላፊ ታደሰ ወረደ ገለጹ።

አዲስ ማለዳ ዛሬ ከሰጡት መግለጫ እንደሰማችው “የመጀመሪያው እርምጃ በየአካባቢው የታጠቁ ቡድኖችን ማፍረስ እና የተቋቋሙትን ህገ-መንግስታዊ ያልሆኑ አስተዳደሮችን ማፍረስ ነው” ያሉት ጀነራል ታደሰ ወረደ፤ “የፍትህ ስርዓቱን ወደነበረበት መመለስ” በተከታይነት ይሰራል ብለዋል። 

ጄኔራሉ የታጠቁ ሃይሎች ከፌዴራል ሃይሎች ጋር መጠነኛ ግጭት በመፍጠር ሂደቱን እያስተጓጎሉ መሆናቸውንም አብራርተው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግጭት እንዳያገረሽ በሚከላከል መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ኃላፊ እንደገለጹት የፕሪቶሪያ ስምምነት የግዛትን ጨምሮ ሁሉም አለመግባባቶች በህገ መንግስቱ መሰረት መፈታት እንዳለባቸው መደንገጉን አስታውሰዋል።

በራያ አላማጣ አካባቢ የህወሓት ታጣቂዎች ወረራ መፈጸማቸው እየተዘገበ መሆኑን ተከትሎ ነው ይኽ መግለጫ በዛሬው ዕለት መሰጠቱን አዲስ ማለዳ ከክልሉ ቴሌቭዥን ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። የህወሓት ታጣቂዎች ወረራ ፈጽመዋል ቢባልም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ ህወሓት የለበትም ብሏል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ረፋድ ላይ ከመግለጫው አስቀድመው በራያ አላማጣ አካባቢዎች “የህወሓት ታጣቂዎች” በፈጸሙት ጥቃት የተኩስ ልውውጥ መጀመሩ ቢዘገብም ችግሩ “በአማራና ትግራይ ክልል አስተዳደር መካከል አይደለም” ማለታቸውን አዲስ ማለዳ ዘግባ ነበር።

የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲተገበር ለመጠየቅ በራያ አካባቢዎች ቅዳሜና እሁድ የተካሄደውን ሰልፍ ተከትሎ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ኃይሎች ከፈቱት በተባለው ጥቃት  የተኩስ ልውውጥ መጀምሩን ነዋሪዎች እና የአካባቢውን ባለስልጣናት ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎችን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ ህወሓት “አራተኛ ዙር በሕዝባችን ላይ ወረራ ፈፅሟል” ሲል ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ከሷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው “በደቡብ ትግራይ እና በሌሎች የትግራይ ግዛቶች የተፈጠረው ግጭት በፌደራል መንግስትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወይም በህወሓት፤ አሊያም በአማራ እና በትግራይ ክልል አስተዳደሮች መካከል የተፈጠረ አይደለም” በማለት ማጋራታቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።

የአማራ ህዝብ “የቡድኑ ወረራ ቀጥተኛ ሰለባ እና ገፈት ቀማሽ ነው” ያለው አብን፤ የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግስታትም በሕዝብ ላይ “የተቃጣውን የጥፋት ወረራ” በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ጥሪውን አቅርቧል።

ጌታቸው ረዳ አክለውም የፕሪቶሪያውን ስምምነት  የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት በአዲስ አበባ ስብሰባ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ “ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎችን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት የፈጸሙት ነው” ብለዋል።

እንዲሁም ይኽ ክስተት ስምምነቱ ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አያጠያይቅም ያሉት ጌታቸው፤ ሰላምና ንግግር ብቸኛው መንገድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።  

የአማራ ሕዝባዊ ንቅናቄ እንደገለጸው መንግስት እየተፈጸመ የሚገኘውን ጥቃት በዝምታ የሚመለከት ከሆነና “ሕህዝባችን ስርአቱን አምኖ ችግሮች ሁሉ በሕግ አግባብ ይፈታሉ የሚል ቀናኢነቱ ማታለያ ሆኖ ከዋለ፤ “ይህ በራያ ብቻ የማይቆም ይልቁንም የሁሉ ነገር መፍረሻና ማፍረሻ እንዲሆን መንግስት የፈቀደ መሆኑን ታሪክ የሚመዘግበው ሀቅ ነው”።

የአማራና ትግራይ ክልሎች ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ውጥረት ሲነግስ ይኽ የመጀመሪያው አይደለም። በራያ አካባቢ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ወፍላ ወረዳ፣ ዛታ ወረዳ፣ ኮረም ከተማ፣ አላማጣ ከተማ፣ አላማጣ ወረዳ እና ራያ ባላ ወረዳ ናቸው። 

የፌደራል መንግስቱ ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈታ መግለጹን ተከትሎ የሕዝብ አሰፋፈር እና የተፈናቃዮች “ትክክለኛነት” ጉዳይ እያወዘገበ የሚገኝ ሲሆን ለሕዝበ ውሳኔ የማይመች ሁኔታ ለመፍጠር በሚደረግ ጥረት ከአማራ እና ትግራይ ክልሎች ውንጀላዎች ይደመጣሉ። 

Source: Link to the Post

Leave a Reply