የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ ከሰሞኑ “በትግራይ ክልል በኩል የሚታየው አዝማሚያ”፤ “ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ የ…

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ላይ ከሰሞኑ “በትግራይ ክልል በኩል የሚታየው አዝማሚያ”፤ “ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይሆን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ” እንደሆነ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ተናገሩ።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ወሰንን በኃይል እናስከብራለን” የሚል አካሄድ “የትግራይ ሕዝብን ለሌላኛው ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ ነው” ሲሉም አሳስበዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የዶ/ር ለገሰ ጋዜጣዊ መግለጫ “ባለፉት ስድስት ዓመታት የለውጥ ጉዞዎች”፣ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የበጋ ልማት ሥራዎችን የተመለከተ ነበር።

የሰላም እና ደኅንነት ጉዳዮችን ባነሱበት የጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ላይ ከሰሞኑ “በትግራይ ክልል በኩል በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች” ታይቷል ያሉትን “አዝማሚያ” ጠቅሰዋል።

የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት “የትግራይ ክልል ወደ ተሟላ የሰላም ሁኔታ እንዲመለስ እና የትግራይ ሕዝብ መብቶች እንዲከበሩ ፅኑ ፍላጎት” እንዳለው የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ሥራዎችን ማከናወኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

“የፌደራል መንግሥት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተሻገሩ በርካታ ተጨባጭ እርምጃዎችን ወስዷል። ይህ ይበልጥ እንዲጎለብት እና ሰላም እንዲፀና አሁንም ሁሉንም ዓይነት ጥረቶች እና እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል” ሲሉ የፌደራል መንግሥቱን ጥረቶች አብራርተዋል።

ይሁንና ከሰሞኑ “የአማራ አዋሳኝ” በሆኑ አካባቢዎች ይህንን የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ያስቆመውን ስምምነት የሚጥስ “አዝማሚያ” መታየቱን ተናግረዋል።

ዶ/ር ለገሰ፤ “ታይቷል” ያሉት አዝማሚያ ምን እንደሆነ በግልፅ ባይጠቅሱም የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን ከሚያወዛግቡ አካባቢዎች መካከል በሆኑት በራያ ወረዳዎች ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የተኩስ ልውውጦች ተደርገዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልል ስር መሆኑት እነዚህን አካባቢዎች የሚያስተዳድሩ አካላት “ከትግራይ ክልል መጥተዋል” የሚሏቸው ታጣቂዎች ተኩስ እንደከፈቱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰንብተዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ በዛሬው መግለጫቸው፤ “የሚነሱ ጥያቄዎች እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በኃይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ ካለፈው ስህተት አለመማርን ያመለክታል” ብለዋል።

መጋቢት 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply