የአማራ ክልላዊ መንግሥት “ጠባብ ግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ፍላጎትን የሕዝብ አስመስለው በማቅረብ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ትርክት በመንዛት ቡድናዊ ጥቅምን ማስቀጠል አይቻልም” ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በመግለጫውም “በትላንት የታሪክ ምርኮኞችና በነገው ተስፋችን ቁማርተኞች ሕልውናዋን የማታጣ ሃገር መገንባት ከሁላችንም የሚጠበቅ ኀላፊነት ነው” ብሏል፡፡

የትላንት ታሪካችን መጥፎ ብቻ አይደለም አይደለም ያለው መግለጫው መታወቅ ያለበት ሃቅ የትላንት መጥፎ ታሪክ ጠበቃዎች አይደለንም ብሏል፡፡

አሁን አሁን የትላንት ታሪክ ምርኮኛ ፖለቲከኞች ታሪክን እያዛቡ በማመንዠክ ዛሬያችንን ስለነገው ተስፋችን ከመሥራት ይልቅ ስለትላንቱ ተረከ-ታሪክ እሰጥ-አገባ መቆም የትውልዳችን ወትሯዊ ውሎ ሲሆን ይስተዋላል ያለው መግለጫው

የትላንት ታሪክ ምርኮኛዎች ትናንትን ከዛሬ በዉል ለይቶ ወደ ነገ መሻገር ሲሳናቸዉ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ቁሞ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰብን ማመንዠክ ልዩ ክህሎትና መገለጫቸው እየሆነ መምጣቱንም አብራርቷል፡፡

በዚህም ልብስና ወንበር እየቀየሩ በተቀናጀ እና በተናበበ መንገድ የሚረጩት መርዛማነቱ ከልብስና ወንበራቸው ጋር አብሮ ያልተቀየረ የከፋፋይነት ፖለቲካዊ ብያኔና ፍረጃ የሀገርና የሕዝብን ሰላም፣አብሮነት እና ልማት ምን ያህል እያቀነጨረው እንደሆነ ሊገነዘቡት እንዳልቻሉ ወይም እንዳልፈለጉ ገልጧል፡፡

በሕዝብ ትከሻ ላይ ተንጠልጥሎ ስሁት ትርክት እየነዙ ደም አፋሳሽ በሆነ መንገድ በሥልጣን ለመኖር ወይም ወደ ስልጣን ለመምጣት ቅጽበታዊ እድል ለማግኘት ካልጠቀመ በስተቀር ለሀገር አይጠቅምም ያለው መግለጫው

በሰፊ ሀገርና በታላቅ ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ የጠበበ ግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ፍላጎትን የሕዝብ አስመስሎ በማቅረብ፣ ቡድናዊ ጥቅሜን አስቀጥላለሁ ብሎ ማመን የፖለቲካ ቁማር ቋሚ ሰልፈኝነትን ያስረዳል ሲል በመግለጫው አብራርቷል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply