የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ባሉ ግጭቶች ዙሪያ እየመከሩ ነው

የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ በአማራና ኦሮሚያ  ክልሎች ባሉ ግጭቶች ዙሪያ እየመከሩ ነው

መልዕክተኛው የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻፀምን ይገመግማሉ ተብሏል

የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰቱ  ግጭቶች በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮችና   በመንግሥትና  በህወሓት መካከል የተደረሰው ስምምነት አፈጻጸም  ግምገማ ዙሪያ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መግለጫ ላይ እንደተጠቆመው፤ ልዩ መልዕክተኛው  በአሁኑ ጊዜ በተባባሰው የአማራ ክልል ግጭትና ዓመታትን ባስቆጠረው የኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት ዙሪያ ሰላም ለማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር  ይመክራሉ ተብሏል፡፡
በትግራይ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም በተደረገው ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው አምባሳደር ማይክ ሐመር፤ ደም አፋሳሹን የሰሜን ኢትዮጵያን የእስር በርስ ጦርነት ያስቆመውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፈጻጸም በተመለከተ በአፍሪካ ኅብረት አስተናጋጅነት፣ ከየካቲት 28 አስከ መጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚካሄደው ግምገማ ላይ ተሣታፊ እንደሆኑም ተገልጿል። ከተፈረመ አንድ ዓመት ያለፈውን የፕሪቶሪያው ስምምነት የአፈጻጸም ሂደት በተመለከተ የስምምነቱ አሸማጋዮችና ታዛቢዎች የሚሳተፉበት ግምገማ እንደሚካሄድ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ልዩ መልዕክተኛው  አምባሣደር ሐመር፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር  በመገናኘት  በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ያለውን ግጭት ለማብቃት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማፋጠን በሚያስችሉ ሁኔታዎችንና ግጭቱን በድርድር ለመፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ የአሜሪካው  የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የአምባሳደር ሐመርን ጉዞ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ካለፈው አመት ሐምሌ ወር ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በሚገኘውና  ከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ በገባው የአማራ ክልል ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት መባባሱን ተከትሎ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት  አሜሪካ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ  እንደምትገኝም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በመንግሥትና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ በሚጠራው ታጣቂ ኃይል  መካከል  ያሉ ግጭቶችን ለማስቆምና ሰላም ለማውረድ የተደረጉ ሙከራዎች ውጤት ሳያመጡ መቅረታቸው አይዘነጋም፡፡ የፊታችን ረቡዕ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው ውይይት፤ ግጭት ውስጥ ያሉ ሃይሎች ወደ ሠላማዊ  መንገዶች የሚመጡበትንና ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዕድል ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply