የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዩኤስ ኤድ በኢትዮጵያ ያለዉን የምግብ ስርዓት ለመደገፍ በ86 ሚሊየን ዶላር የሚተገበሩ ሁለት የግብርና ፕሮጀክቶችን ይፋ አደረገ፡፡

የዩኤስ ኤድ የኢኮኖሚ ዕድገት ቢሮ ዳይሬክተር አምበር ኬኒ እና የግብርና ሚኒስቴር ድኤታ ዶ/ር መለስ መኮንን ፕሮጀክቶቹን በጋራ ይፋ አድርገዋል፡፡

ሁለቱ የግብርና ፕሮጀክቶች ‹‹ግብርናን መቀየር›› እና ‹‹የኢትዮጵያ የዘር ስርዓት›› የተሰኙ ሲሆን ፤በ77 ሚሊየን ዶላር እና በ9.5 ሚሊየን ዶላር የሚተገበሩ መሆናቸዉም ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቶቹ ገቢን ማሳደግ እና በአገሪቱ ያለዉን የተመጣጠነ ምግብ ዕጥረት ደረጃ ይቀንሳሉ ተብሏል፡፡

‹‹ግብርናን መቀየር›› የተሰኘዉ ፕሮጀክት ለ5 ዓመታት የሚተገበር ሲሆን የኢትዮጵያን የግብርና እና የምግብ ስርዓት የሚደግፍ ይሆናል ነዉ የተባለዉ ፡፡

ፕሮጀክቱ 7 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎችን በተለይ ሴቶች እና ህጻናትን የአመጋገብ ሁኔታቸዉን ይለዉጣል የተባለ ሲሆን፤በአገሪቱ በሚገኙ በ1መቶ32 ወረዳዎች ላይም ይተገበራል ተብሏል፡፡

ይህ ፕሮጀክት የእንሰት ማቀነባበሪያ ማሽኖችን በመጠቀም የእንሰት አምራቾች የምርት መጠን እንዲጨምር፣ የምግብ ብክነት እንዳይኖር እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲመረት ያግዛል ነዉ የተባለዉ፡፡

የኢትዮጵያ የዘር ስርዓት የተሰኘዉ ሁለተኛዉ ፕሮጀክት ደግሞ ጥራታቸዉን የጠበቁ ምርጥ ዘሮችን ለአገር ዉስጥ ገበያ በማቅረብ ፤ ትንንሽ እርሻ ያላቸዉ ሰዎች የፈለጉትን የዘር ዓይነት በጥራት እንዲያገኙ የሚረዳ ነዉ ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በ 8ክልሎች በሚገኙ 20 ወረዳዎች ዉስጥ የሚተገበር ይሆናል፡፡

ሁለቱ ፕሮጀክቶች ቀጣይነት ያለዉ ፣ጠንካራ፣ አካታች የሆነ የግብርና እና የምግብ ስርዓት እንዲኖር ከአግሪ-ቢዝነስ ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከሌሎች የግብርና አጋሮች ጋር  በጋራ የሚሰሩ መሆናቸዉም ተገልጿል፡፡

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply