የአሜሪካ ኤምባሲ ማሳሰቢያ መሠረተ ቢስ ነው – የአአ አስተዳደር

https://gdb.voanews.com/62b4f2f9-cf03-4cbc-982a-8ecf4f5490c1_tv_w800_h450.jpg

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ላይ “በተለያየ መልኩ ታደርገዋለች” ካለው ጫና “ትቆጠብ” ሲል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች አገልግሎት አሳስቧል። 

የኮምዩኒኬሽንስ ሚኒስትር ደ’ኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ዛሬ መግለጫ ሲሰጡ “አዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል” በሚል የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ያወጣው መግለጫ “በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ነው” ብለዋል።

ይህን ክስ በተመለከተ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባለስልጣን ለቪኦኤ በኢሜል በሰጡት ምላሽ “በውጭ ሀገር ያሉ የአሜሪካ ዜጎች ደህንነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ ኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካ ዜጎች ባገኙት በረራ እንዲወጡ ማሳሰባችንን እንቀጥላለን” ብለዋል። 

በተያያዘ ዜና “የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትና ሌሎች ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ነው” ያሉትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ቁጥራቸው የበዛ ሰልፈኞች አዲስ አበባ ውስጥ አሜሪካና ብሪታንያ ኤምባሲዎች በር ላይ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ “እየተባባሰ ነው” ባሉት ግጭት ምክንያት ዜጎቻቸው ፈጥነው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የእንግሊዝ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ማሳሰባቸውን ሮይተርስ ትናንት ዘግቧል።

ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ ባወጡት ማሳሰቢያ “በመጭዎቹ ቀናት ውጊያው ወደ አዲስ አበባ ሊቃረብ ስለሚችል የእንግሊዝ ዜጎች ከሃገሪቱ ለመውጣት ሊቸገሩ ይችላሉ” ብለዋል።

“ላለመውጣት የመረጣችሁ ደግሞ ቢያንስ ለጥቂት ሳምንታት ባላችሁበት ቦታ ደኅንነታችሁ በሚጠበቅበት ሁኔታ ለመጠለል የሚያስችላሁን ዝግጅት እንድታደርጉ እንመክራለን። ወደፊት ከኢትዮጵያ መውጣት የሚቻልበት አማራጭ ስለመኖሩ ማረጋገጫ መስጠት አንችልም” ሲሉ አክለዋል ሚኒስትሯ።

 

Source: Link to the Post

Leave a Reply