የአሜሪካ ወታደሮችን ገድያለሁ ያለው ታጣቂ ቡድን አሜሪካ ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማቆሙን ገለጸ

በዮርዳኖስ ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉበትን ጥቃት እንደፈጸመ የተጠረጠረ በኢራቅ የሚገኝ ታጣቂ ቡድን አሜሪካ ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት ማቆሙን አስታወቀ።

ካታይብ ሄዝቦላህ የተባለው እና ከኢራን ጋር ግንኙነት ያለው ታጣቂ ቡድን ለዚህ ውሳኔው ምክንያቱን ሲገልጽ “የኢራቅ መንግሥት ሊደርስበት የሚችለውን አሳፋሪ ምላሽ ለመከላከል ነው” ብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ዕሁድ በዮርዳኖስ የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ሰፈር ላይ ለተፈጸመው እና ለሦስት ወታደሮች ሞት ምክንያት ለሆነው ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ መወሰናቸውን ገልጸዋል። ሆኖም አጸፋው በምን መልኩ ይሆናል የሚለውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

አሜሪካ በተደጋጋሚ የአጸፋ ምላሹ ወታደራዊ ጥቃት ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥታለች።

ከእሁዱ ጥቃት ጀርባ ነበርኩ ያለው ካታይብ ሄዝቦላህ የጸጥታ ዘርፍ ዋና ጸሀፊ አቡ ሁሴን አል ሃሚዳዊ ባወጣው መግለጫ “በኢራቅ መንግሥት ላይ የሚደርሰውን አሳፋሪ ምላሽ ለመከላከል በሚል ወራሪ ኃይሎች ላይ የምንወስደውን እርምጃ ብናቋርጥም በጋዛ ህዝባችንን መከላከል እንቀጥላለን” ብሏል።

ባለፈው ዕሁድ በዮርዳኖስ እና ሶሪያ ድንበር አከባቢ የተፈጸመው ጥቃት በኢራን ሰራሽ ድሮን እንደሆነ ተዘግቧል።

በዚህ ጥቃት ሶስት ወታደሮች ከመገደላቸው በተጨማሪ በርካታ የአሜሪካ ወታደሮችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አሜሪካ ይህንን ጥቃት የፈጸሙት በኢራን የሚደገፉ ኃይሎች ናቸው ብትልም ካታይብ ሄዝቦላህ የጥቃቱ ፈጻሚ ነው ብላ አልደመደመችም።

ታጣቂ ቡድኑ አሜሪካ ላይ ጥቃት መሰንዘሬን አቁሜያለሁ ማለቱን ተከትሎ የፔንታገን ቃል አቀባይ
በሰጡት መግለጫ “ድርጊት ከቃል በላይ ይናገራል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ቃል አቀባዩ ፓት ራይደር አክለውም ድርጊቱ ከባድ መዘዝ እንደሚያስከትልም አክለዋል።

ኢት ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጥር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply