የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ በኦነግ የፖለቲካ ሹም በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ጠይቋል። መስሪያ ቤቱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የግጭት አዙሪትን…

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ በኦነግ የፖለቲካ ሹም በቴ ኡርጌሳ ግድያ ላይ “ሙሉ ምርመራ” እንዲደረግ ጠይቋል።

መስሪያ ቤቱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የግጭት አዙሪትን ለመቀልበስ ፍትህ እና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚያስፈልግ ገልጧል።

ሂውማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፣ የበቴ ኡርጌሳ ግድያ “ተዓማኒ ምርመራ” ያስፈልገዋል ብሏል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፣ የአቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በራሱ ማጣራት እንደሚያደርግ አመልክቶ፤ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ገለልተኛ እና ሚዛናዊ ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአቶ በቴ ኡርጌሳን ግድያ በፅኑ እንደሚያወግዝ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ገልጻል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት፣ በኦነግ አመራር አባል በቴ ኡርጌሳ ግድያ መንግሥትን ተጠያቂ የማድረጉ ፕሮፓጋንዳ “በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም” ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አጣጥሏል።

ምርመራ ባልተደረገበት ሁኔታና ወንጀል ፈጻሚው ገና ባልታወቀበት ሁኔታ ክስተቱን ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ የሚጠቀሙ ኃይሎች መኖራቸውን በማመልከት አጥብቆ አውግዟቸዋል።

” ከመንግስት ጋር የአቋም ልዩነት ስላላቸውና የፖለቲካ አቋማቸው ስለሚለይ ብቻ ግድያው በመንግሥት አካል እንደተፈፀመ ተደርጎ የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ” ብሏል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፥ ” የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው የፖለቲካ ኃይሎች መንግሥትን ለግድያው ተጠያቂ በማድረግ ይህንን ሁኔታ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው ” ሲል ወቅሷል።

መንግሥት በአቶ በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ ውጤቱን ለህዝብ እንደሚያሳውቅም ባወጣው መግለጫ ቃል ገብቷል።

የፀጥታ ኃይሎች የግድያውን ፈፃሚ በህግ አግባብ መርምረውና አጣርተው እስካላሳወቁ ድረስ ” ይህ አካል ነው ኃላፊነት የሚወስደው ” ብሎ መናገር እንደማይቻል ጠቁሟል።

ማህበረሰቡ ገና ውጤቱ ሳይታወቅ እየተካሄዱ ካሉት ” እከሌ ነው የገደለው ” ከሚሉ ፕሮፖጋንዳዎች ራሱን መጠበቅ አለበትም ብሏል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ሚያዝያ 03 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply