የአምስት ቀን ልጇን አንቃ የገደለችው ተከሳሽ በ8 ዓመት እስራት ተቀጣችየ5 ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን በሻሽ አንገቱን በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገችው ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ5…

የአምስት ቀን ልጇን አንቃ የገደለችው ተከሳሽ በ8 ዓመት እስራት ተቀጣች

የ5 ቀን ዕድሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን በሻሽ አንገቱን በማነቅ ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገችው ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ5 ወር ጽኑ እስራት እንድትቀጣ ተወሰኖባታል፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳዉ ፤ ተከሳሽ ሰብሪያ ወይንም በሌላ ሥሟ ፋይዛ በድሩ ሽፋ የተባለች ግለሰብ፤ ከመስከረም 10 እስከ 11/2014 ባለውና ወንጀሉ የተፈጸመበት ሰዓት በውል

በማይታወቅበት ጊዜ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 540 ሥር የተመለከተውን ተላልፋ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ቦታው አለም ባንክ አካባቢ ጓደኛዋ ተከራይታ በምትኖርበት ቤት ውስጥ የጓደኛዋን ወደ ሥራ መሄድ ተጠቅማ የአብራኳ ክፋይ በሆነው ልጇ ላይ የጭካኔዋን ጥግ አሳይታለች፡፡

በክስ መዝገቡ ላይ በዝርዝር እንደተብራራው ተከሳሽ፣ በፆታ ወንድ የሆነዉንና የ5 ቀን ዕደሜ ያለው ጨቅላ ህፃን ልጇን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በሻሽ አንገቱን አንቃ ህይወቱ እንዲያልፍ ካደረገች በሗላ በብርድ ልብስና በፍራሽ ጠቅልላ በማስቀመጥ ቤቱን ዘግታ ከአከባቢው ብትሰወርም በተደረገባት ክትትል በቁጥጥር ሥር ውላ የወንጀል ምርመራ ተደርጎባት ወንጀሉ ስለመፈጸሙ ተረጋግጦ በግለሰቧ ላይ ክስ ተመስርቶባታል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከሳሽ ላይ በመሰረተው ክስ ፍርድ ቤት ቀርባ ክርክር ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ሐምሌ 14 ቀን 2014 በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ5 ወር ፅኑ እስራት እንድትቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ መስጠቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ነሐሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/channel/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Website https://ethiofm107.com/

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።

ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply