
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ያሬድ በጸጥታ አካላት አፈና ተፈጸመባቸው፤ ወደየት እንደተወሰዱ አድራሻቸው አልታወቀም። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ ያሬድ አሰላ ከሚገኘው መንበረ ጵጵስናቸው ዛሬ ምሽት 3:30 በፀጥታ ኃይሎች ተወስደዋል። ለምን እና ወዴት እንደተወሰዱ የታወቀ ነገር የለም። ብፁዕነታቸው ከቀናት በፊት በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት የተሠራውን የማኅደረ ስብሐት በዓታ ለማርያም መልእክተ ዮሐንስ የአዳሪ አብነት ትምህርት ቤትን መመረቃቸው ይታወቃል። በተመሳሳይ ማህበረ ቅዱሳን ብሮድካስት እንዳጋራው በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት ሻሸመኔ ከተማ በሕገ ወጥ የተሾመው ቡድን መንበረ ጵጵስና እና ቤተ ክርስቲያን ሰብረን እንገባለን በማለት በምእመናን ላይ ስጋት መፍጠሩን ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የሲዳማ፣ ጌዲዮ፣ አማሮ፣ ቡርጂና ምዕራብ አርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አሳውቀዋል። ከሰሞኑን የሀገረ ስብከቱ አገልጋዮች ያለምክንያት እየታሰሩ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ይህንንም ለሚመለከተው የዞን ፀጥታ አካል ለማሳወቅና ጥበቃ እንዲያደርጉ ብንደውልም፣ መልእክት ብንጽፍም ሊመልሱልን አልቻሉም ብለዋል። በመጨረሻም ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ መልእክት አስተላልፈዋል።
Source: Link to the Post