የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የጨንቻ አፕል እና የአዊ ድንች ምርቶችን ብራንድ ተደረጉ

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን አነሳሽነት በአይነታቸው የተለዩና በኀብረት ሥራ ማህበራት አባላት የሚመረቱ “የአርባ ምንጭ ሙዝ”፣ “የአዊ ድንች” እና “የጨንቻ አፕል” ምርቶች አዳዲስ የብራንድ መለያዎችን በይፋ የማስተዋወቅ ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት በስካይ ላይት ሆቴል በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህ የግብርና ምርቶች ዋና ዋና ፈተናዎች በአገር አቀፍ ገበያ በስፋት ተደራሽ አለመሆን፣ ደካማ የግብይት ትስስር፣ በገበያ መሰረተ ልማት እጦት እና በእሴት ሰንሰለት ውስጥ ጥቂት የሚባሉ ነጋዴዎችና ደላሎች እንዳሻቸው የዋጋ ተመን በማውጣት ገበያውን በሚቆጣጠሩበት የተዛባ የግብይት ሥርዓት በመገደባቸው አምራቹም ሆነ ሸማቹ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ እንዳደረጋቸው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን ከግብርና ሚንስቴር እና ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እነዚህን ችግሮችን ለመፍታት ምርቶቹ በሚገኙበት ክልሎች ያሉ ኀብረት ሥራ ማህበራትን ማጠናከር፣ ምርታማነትን ማሳደግና የምርቶቹን የግብይት ስርዓት ማዘመን የሚሉ ቁልፍ ተግባራትን ያለመ ፕሮግራም ቀርጾ በቅርቡ ወደ ተግባር መግባቱን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ምርቶቹን ብራንድ ማድረግ በክልሎቹ የሚመረቱ ሙዝ፣ አፕልና ድንችን በብዛትና በጥራት በማምረት ያለውን ሰፊ የገበያ መዳረሻዎች ለመጠቀምና የተዛባ የገበያ ሥርዓቱን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ ኀብረት ሥራ ኮሚሽን ለእነዚህ ምርቶች ጠንካራ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች በመፍጠር ታላቅ ዕውቅና እንዲጎናጸፉ ለማስቻል በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እና በአማራ ክልሎች ከሚገኙ እንደ ኀብረት ሥራ ማህበራት፣ የኀብረት ሥራ ማስፋፊያ ኤጀንሲዎች፣ የግብርና ቢሮዎችና የዞን አስተዳደሮች ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በከፍተኛ ትጋት እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ምርቶቹን አምርተው ለገበያ የሚያቀርቡት የግብርና ኀብረት ሥራ ማህበራት በምርት እሸጋ፣ በመሰረተ ልማት፣ ጥራት ባለው አገልግሎት አሰጣጥ፣ በምርት ማጓጓዣ፣ በፕሮሞሽንና ማስታወቂያ ለመሳሰሉ ስራዎች ትኩረት በመስጠት እንደሚሰሩ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

የአርባ ምንጭ ሙዝ፣ የአዊ ድንች እና የጨንቻ አፕል ምርቶች አዳዲስ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች ምርቶቹ ሰፊ የገበያ መዳረሻዎች እንዲኖራቸው በማድረግ የምርቶቹ ዋጋን ለማረጋጋት እና የአርባ ምንጭ ሙዝ በተለየ ሁኔታ በሂደት ዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር እንዲያገኝ በመርዳት የአምራቹን ኑሮ ከማሻሻሉ በተጨማሪ አገራዊ ፋይዳ ሊያመጣ እንደሚችል ታምኖበታል፡፡

የእነዚህ ምርቶች የብራንድ መለያዎች ይፋ በሆኑበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የምርቶቹ የብራንድ ስያሜዎች፣ አዳዲስ አርማዎችና መሪ ቃሎች በይፋ እንዲተዋወቁ ከመደረጉ ሌላ ስለ ምርቶቹ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ሙዝ በኢትዮጵያ በስፋት ዕውቅና ካላቸው የሙዝ ዝርያዎች ቀዳሚው ሲሆን በኦርጋኒክነቱ፣ በተለየ ጣዕምና ጥራቱ እንዲሁም ባለው ረጅም የቆይታ ግዜ ይወደዳል፡፡

የጨንቻ አፕል እንደዚህው ባለው ልዩ ጣዕም፣ አነስተኛ የአሲድ መጠን፣ በውስጡ በያዘው የፈሳሽ ይዘቱ፣ ጥቅጥቅ ያለ መሆኑና ሲበላ ለጥርስ ምቾት ያለው መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡

የአዊ ድንች ደግሞ የተጠቀጠቀ፣ ጥሩ ቅርጽና ልስላሴ ያለው ሲሆን በተለያየ የምግብ አይነት ተቀቅሎ፣ ተጋግሮና ተጠብሶ ሊበላ የሚችል ሃይል ሰጭና ሌሎች የምግብ ንጥረ ነገር ይዘቶች የያዘ ነው፡፡

በሦስቱ የግብርና ምርቶች ማለትም በሙዝ 140 ሺህ 355 አባላት ያሏቸው 30 መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፣በአፕል 242 ሺህ 906 አባላት ያቀፉ 12 መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲሁም በድንች 69 ሺህ 984 አባላት ያቀፉ 29 ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡

በቅርቡ እንደዚሁ ስትራቴጂክ ተብለው በተለዩ የግብርና ምርቶች ላይ የብራንድ እሴቶችና መለያዎች የመፍጠር ሥራ የሚቀጥል ሲሆን፤ በዚህም መሰረት በሶማሊ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች በቅደም ተከተል የሚገኙት የፍየል፣ ማንጎና ቀይ ሽንኩርት ምርቶች ብራንድ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

በዛሬው ዕለት እየተከናወነ በሚገኘው ምርቶቹን የማስተዋወቅ ሥነ ሥርዓት ላይም፤ የፌደራል እና የክልል የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች እና አምራች ማህበራት እየተሳተፉበት ይገኛል።

  

Source: Link to the Post

Leave a Reply