የአስተዳደራዊ እና የመዋቅር ጥያቄዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት እንዳይሆኑ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ኢሰመኮ አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተውን የጸጥታ መደፍረስና ያስከተለውን ጉዳት ከአካባቢው ነዋሪዎች በቀረበለት አቤቱታ መነሻነት ከጥቅምት 20 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በቦታው በመገኘት ጭምር ምርመራ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡

አሁንም በአካባቢው ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታም በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡

ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች እና ምስክሮች ጋር 22 ቃለ-መጠይቆች ማድረጉን፣ ከጉራጌ ዞን፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር እና ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ በዞን እና በልዩ ወረዳ ደረጃ ከሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኘውን የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎችን አነጋግሯል፣ በተጨማሪም ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 2 የቡድን ውይይቶች እንዳካሄደም ኮሚሽን ጠቁሟል።

እንዲሁም ዘረፋ እና ውድመት ደርሶባቸዋል የተባሉ የግል እና የመንግሥት ተቋማትን ኮሚሽኑ ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፤ ተጎጂዎች ሕክምና ካገኙባቸው የሕክምና ተቋማት የሕክምና ማስረጃዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሰነድ ማስረጃዎችን አሰባስቧል።

በጉራጌ እና በቀቤና ማኅበረሰብ መካከል ከዚህ በፊትም የተለያየ መጠን ያለው ግጭት እና የሰላም ስምምነት ጥረት የነበረ ሲሆን፤ በተለይ ከቀቤና የልዩ ወረዳነት ምሥረታ ጋር በተያያዘ እና የልዩ ወረዳው መቀመጫን በተመለከተ በሁለቱ ማኅበረሰቦች አስተዳደሮች መካከል አለመግባባቱ እየተካረረና የግጭት አደጋው እየጨመረ መጥቶ እንደነበር መረዳት ተችሏል ነው ያለው።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች አሁንም ዘላቂ መፍትሔ ያልተሰጣቸው የመዋቅር እና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላም እና ደኅንነት እጦት እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ሆነው መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ ስለሆነ፤ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ቅሬታና ጥያቄ የቀረበባቸውን አካባቢዎች ሁሉ ተዓማኒ በሆነና ተቀባይነት ባለው ሂደት በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመቻቹ ይገባል” ብለዋል፡፡

ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “በወልቂጤ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከሰተው ሁከት እና የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በመቀናጀትና ተገቢውን ማጣራት በማድረግ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ተጎጂዎች ሊካሱ ይገባል” ብለዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply