የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ወራት ተራዘመ

ላለፉት ስድስት ወራት በዋነኛነት በአማራ ክልል ተፈጻሚ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ አስተላለፈ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመራዘም ለምክር ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ የጸደቀው፤ በሁለት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ እና በሶስት ጽምጸ ተዐቅቦ ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያጸደቀው ነሐሴ 8፤ 2015 ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ያሳለፈው፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ያለውን “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ”፤ “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ ተሸጋግሯል” በሚል እንደነበር ይታወሳል።

በዛሬው የፓርላማ ልዩ ስብስባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ ያቀረቡት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ናቸው። ይህን ተከትሎ የፓርላማ አባላቱ “ሰፊ ውይይት” ማድረጋቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ቢያስታውቅም፤ በስብሰባው የተነሱ ነጥቦችን ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መራዘም ተከትሎ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን እንዲከታተል በፓርላማ የተሾመው መርማሪ ቦርድ የስራ ዘመንም በተመሳሳይ ሁኔታ ተራዝሟል። ሰባት አባላት ያሉትን የዚህን መርማሪ ቦርድ የስራ ዘመን ለማራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ፤ ሁለት የፓርላማ አባላት ቢቃወሙትም በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Source: Link to the Post

Leave a Reply