የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ የኤርትራ ጦር ፈፅሟል የተባለውን የመብት ጥሰት አጣራለሁ ቢልም አመነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በዚሁ ጦር ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸውን ለማወቅ ችያለሁ ብሏል፡፡

በወርሃ ጥቅምት መገባዳጃ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ተፈፅመዋል የተባሉትን ወንጀሎች መንግስት እያጣራ ሰለመሆኑ ገልፆ ነበር፡፡መግለጫው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በጋራ ሆነው ጉዳዩን እያጣሩት ስለመሆኑም አስታውቋል፡፡

ይሁንና ተቋሙ ይህን መግለጫ ካወጣ በጥቂት ሰዓታት ልዩነት ውስጥ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋርቋሪ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት በአክሱም ከተማ የጅምላ ግድያዎች መፈፀማቸውን ከሳተላይት ምስሎችና ከዐይን እማኞች መረዳት ችያለሁ ብሏል፡፡41 ከጥቃቱ የተረፉና የዐይን እማኞች ነገሩኝ እንዳለው የኤርትራ ጦር በህዳር 28 እና 29 2020 እ.አ.አ. አክሱም ከተማን ለመያዝ በፈፀመው ወረራ በመቶዎች የሚቆጠሩት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፡፡

የአምነስቲ የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮሲ ሙቼና በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ሲሉ የጠሩት የጅምላ ግድያ እስካሁን ጦርነቱን ተከትለው ከተሰሙት ሁሉ የከፋ ነው ሲሉ ኮንነውታል፡፡ይህ በአክሱም ከተማ የተፈፀመውን ግድያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲያጣራ የጠየቁት ዳይሬክተሩ የወንጀሉ ፈፃሚዎችም በህግ እንዲጠየቁና ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸውም አስፈላጊው ሁሉ ካሳ እንዲከፈላቸው አሳስቧል፡፡ ሙቼና ” አምነስቲ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስት በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፎች የሚቀርቡበት መንገድ እንዲመቻች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተቋርቋሪ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን ወደ ስፍራው ገብተው እንዲጎበኙና እንዲዘግቡ ይጠይቃል፡፡’’ ብለዋል፡፡
ይህ የመቶዎች የጅምላ ግድያ የተፈፀመው ዓመታዊው የአክሱም ፅዮን ክብረ በዓል ከመከበሩ አስቀድሞ መሆኑንም ተቋሙ ይፋ አድርጓል፡፡ አንድ የ22 ዓመት ወጣትን ምስክርነት ተቀብያለሁ ያለው አምነስቲ የኤርትራ ጦር ሰራዊት በውትድርና በጣም የሰለጠኑ ናቸው፡፡
ከእነርሱ በአንፃሩ የቆሙት ምንም እንኳን መሳሪያ ቢታጠቁም አተኳኮሱን እንኳ አያውቁትም፤ ከዚህ በኋላ ጦሩ መሣሪያ የታጠቁትን ጨምሮ ሌሎች ንፁሃንንም ሳይለይ እንደገደለ ተናግረዋል፡፡
እንደ አምነስቲ ከሆነ የመቶዎቹ የጅምላ ግድያ ቀብር የተፈፀመው በህዳር 30 ቀን 2020 እ.አ.አ. ነው፡፡
ከዚህ የአምነስቲ ሪፖርት በኋላ መግለጫ ያወጣው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ይህ ሪፖርት ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ነው ብሏል፡፡
በኮሚሽነሩ ዶክተር ዳኒኤል በቀለ የወጣው አጭር መግለጫ እንደሚለው ይህ የአምነስቲ ሪፖርት ኮሚሽኑ በክልሉ ለሚያደርጋቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ አጋዥ ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም በክልሉ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሪፖርት ማውጣቱን ያስታወሰው ኮሚሽኑ ወደፊት ሙሉ ሪፖርቱን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply