You are currently viewing የአሸባሪው ሸኔ ተደጋጋሚ ወረራ ያስከተለው ውድመትና ማህበራዊ ቀውስ በገለልተኛ ተቋማት እንዲታይ እና የሽብር ቡድኑን ወደ ወረዳው እየሳቡ የሚያስገቡት እጆች ማንነታቸው ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ…

የአሸባሪው ሸኔ ተደጋጋሚ ወረራ ያስከተለው ውድመትና ማህበራዊ ቀውስ በገለልተኛ ተቋማት እንዲታይ እና የሽብር ቡድኑን ወደ ወረዳው እየሳቡ የሚያስገቡት እጆች ማንነታቸው ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ…

የአሸባሪው ሸኔ ተደጋጋሚ ወረራ ያስከተለው ውድመትና ማህበራዊ ቀውስ በገለልተኛ ተቋማት እንዲታይ እና የሽብር ቡድኑን ወደ ወረዳው እየሳቡ የሚያስገቡት እጆች ማንነታቸው ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን እንቅስቃሴ እውን ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አስታወቀ። ሕዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም አሻራ ሚዲያ ፣ ባህርዳር በሸዋ የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ የሰጠው የአቋም መግለጫ:_ የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ኅዳር 18/ 2015 ዓ.ም ባአካሄደዉ አስቸኳይ ስብሰባ በተለያዩ ጊዜያት አሸባሪዉ ሸኔ ወረዳዉን ለመቆጣጠር ያደረገዉን ሙከራ ፊት ለፊት ሲፋለሙ አንድያ ነፍሳቸውን አሳልፈው ለሰጡ ጀግኖች ወንድሞቻችንን በማሰብ የአንድ ደቂቃ የሂሊና ፀሎት በማድረግ ለመላው ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ወዳጆቻቸው ፈጣሪ መፅናናትን እንድሰጣቸዉ ተመኝቷል። የደርግ መንግስት ተገርስሶ ኢህአዴግ ሃገራችንን ማስተዳደር መጀመሩን ተከትሎ ክልለሎች ሲካለሉ ደራ ወረዳ ቀደሞ ከነበረበት የመርሐቤቴ አውራጃ ተነጥሎ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መካተቱ ይታወቃል። ደራ ወረዳ የሁለት ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆኑ እየታወቀ የህዝቡን ፍላጎት ባልጠበቀና በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ መብት በማያስከብር መልኩ ወረዳውን ሙሉ በሙሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ማካለሉ ፍትሃዊ አለመሆኑ በአማራው ማህበረሰብ ዘንድ ተቃውሞ ሲቀርብበት እንደቆየ የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም። ከግንቦት 17/1984 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በ3 ምዕራፎች የተከፈሉ ጥያቄዎችን ስናቀርብ ቆይተናል። በዚህ ሰላማዊ የትግል ሂደት በርካታ ታጋዮች ለሞት፣ ለእስር እና መሰል እንግልቶች ተፈፅሞባቸዋል። ይሁን እንጂ ህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ጭቆና እየተባባሰ በመምጣቱ ህዝቡ ሰፊ ውይይቶች በማድረግ ጥያቄውን በውክልና የሚያቀርቡለትና የሚከታተሉለት ከህዝብ የተውጣጣ ኮሚቴ ማዋቀር ችሏል። የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ በተቀናጀ፣ በተደራጀና በተጠና መልኩ ድሮ ከነበሩት ኮሚቴዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር መስከረም 2/2011 ዓ.ም የህዝብ ውክልና ተሰጥቶት የደራ አማራ ያነሳቸውን ጥያቄዎች አነግቦ ትግሉን በሰላማዊ እና ህጋዊ ሂደቱን በጠበቀ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ኮሚቴው በመጣባቸው ጉዞዎች በርካታ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ከህዝብ የተሰጠውን አደራ ሳያጎድል አሁንም በሰላማዊ ትግል ላይ ይገኛል። ህዝቡ ያቀረበውም ጥያቄ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሂደቶች ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ መሰረታዊ ከሆነው ዋነኛ ጥያቄያችን ጎን ለጎን የወረዳችን ህዝብ ተደጋጋሚ በሆኑ ደራሽ ፈተናዎች እየተፈተነ ይገኛል። አሸባሪው ሸኔ ወደ አዲስ አበባ የሚያስኬደውን መንገድ ከዘጋው አንድ አመት እየሆነው ይገኛል። በአሁኑ ሰዓትም የሽብር ቡድኑ ወረዳችን ላይ ገብቶ ባቡ ድሬን ፣ሀርቡ ደሶን፣ አሙማ ገንዶን፣ ኢሉ ዋዩን፣ በቾን፣ መንቃታን፣ ጅሩ ዳዳን ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠረ ሲሆን ቆሮ ግንደበርበሬን፣ አድአ መልኬን፣ ሀቼ ኩሳየን፣ ወሬ ገብሮን እና ዕሮብ ገበያን እንድሁም የጀማን በረሃ በከፊል ተቆጣጥሮ ታጣቂዎችን በማሰልጠን ፣በማደራጀት በመመልመል ላይ ይገኛል። የሽብር ቡድኑ በሚገኝባቸው በነዚህ አካባቢዎች የንፁሃን ሰዎች ጅምላ ጭፍጨፋ፣ እገታና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የንብረት ውድመት እና የማህበራዊ ህይወት መቃወስ እየተፈፀመ ይገኛል። ይህ ሁሉ ውድመት በህዝባችን ላይ እየተፈፀመ እያየ መንግስት ከመንግስትነት የሚጠበቀውን ትንሹን ኃላፊነት እንኳ መወጣት አለመቻሉ ህዝቡ ላለመረጋጋትና ለከፋ ስጋት ተጋልጧል። መከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ ወደ ወረዳው የገባ ቢሆንም እስካሁን ድረስ የሽብር ቡድኑን ካለበት ለማስለቀቅ የተሰራ ወታደራዊ ኦፕሬሽን አለመደረጉ ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። የሽብር ቡድኑ ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ተከታታይ የጥቃት ሙከራዎች ራሱን ያደራጀው ህዝባችን በመንግሥት በኩል በቂ ድጋፍ እየተደረገለት አለመሆኑ ለጠላት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረለት ይገኛል። በተለይም ጥቂት የማይባሉ የዞን እና የወረዳ አመራሮች ከሽብር ቡድኑ ጋር የጥቅም ሽርክና ፈጥረዉ ህዝባችንን በተደጋጋሚ ሲወጋ መረጃ በማቀበል ፣የተደራጀን ሚኒሻ በመበተንና አንድነቱን በመናድ ፣ወጣቱ በራሱ ተነሳሽነት ተደራጅቶ ራሱን የመከላከል ሙከራ ሲያደርግ ወጣቱን መተንኮስ እና የማሸማቀቅ ስራ ሰርተዋል። በሁለት ቢላዋ የሚበሉ የነዚህ ባንዳ ግለሰቦች እንቅስቃሴ አሁንም ድረስ ያልተቋረጠ እንደሆነ እናምናለን። በመሆኑም የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ከላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮችና ሌሎችንም በጥልቀትና በስፋት በማየት ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ኮሚቴው አቋም የያዘባቸው ጉዳዮችን ለህዝባችን ለማሳወቅ ወስኗል። የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ኅዳር 18/2015 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ የሚከተሉትን ባለ 5 ነጥቦች አቋሞችን በመያዝ ስብሰባውን አጠናቋል። 1. እየተንከባለለ እዚህ የደረሰው የደራ አማራ ያቀረበው ጥያቄ እልባት ላይ እንዲደርስ ወቅቱ የሚጠብቀውን የተቀናጀ ስራ መስራትና ሰላማዊ ትግላችንን ከፍ ወዳለ ምዕራፍ ማሸጋገር ዋነኛ አቋማችን ነው። ለዚህ የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ዋነኛ ባለቤቱ የተከበረው የደራ ህዝብ ነውና ከጎናችን በመሆን ለውጤታማነቱ መትጋት አለበት። 2. የአሸባሪው ሸኔ ተደጋጋሚ ወረራ ያስከተለው ውድመትና ማህበራዊ ቀውስ በገለልተኛ ተቋማት እንዲታይ እና የሽብር ቡድኑን ወደ ወረዳችን እየሳቡ የሚያስገቡት እጆች ማንነታቸው ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን እንቅስቃሴ ለማድረግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመስራት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክረን ለመሄድ ወስነናል። ከዚህ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴ ጀርባ ያሉ ግለሰቦች፣ የወረዳና የዞን አመራሮች ተጨባጭ መረጃዎች ቀርቦባቸው በህግ ፊት ተጠያቂ የሚሆኑበት እንቅስቃሴ ጀምረናል። ለዚህ እንቅስቃሴ ውጤታማነት ህብረተሰቡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል። 3. አሸባሪው ቡድን እስካሁን ድረስ ያለቀቃቸው ቀበሌዎች ከአስከፊ ግዞት የሚላቀቁበትን የተደራጀ ህዝባዊ መሰረት ያለው ትግል ለማድረግ ከመንግስት እና ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ከኮሚቴው የሚጠበቀውን ሚና ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም ላይ ደርሰናል። አሸባሪው ቡድን መሰረት ከጣለባቸው ቀበሌዎች ተመቶ ከወረዳው ላይ ሙሉ ለሙሉ እንዲነቀል በአካባቢው ላይ በቂ የመከላከያ ኃይል እንዲገባ የሚጠበቅብንን ጥረት እናደርጋለን። 4. ቀውሱ በፈጠረው ስጋት ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተሰደዱ የወረዳው ነዋሪዎች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ከወረዳው መንግስት ጋር በመቀራረብ ለመስራት ወስነናል። ህዝቡ ከመከላከል ተሸጋግሮ አሸባሪውን ቡድን የማጥቃትና ወረዳችን ዳግም የጥቃት ሰለባ እንዳይሆን ከህዝቡ የተውጣጣ በቂ የተደራጀ ኃይል እንዲኖር አበክሮ መሰራት እንዳለበት የበኩላችንን ሚና እንወጣለን። 5. ኮሚቴው የውስጥ ግምገማዎችን በማድረግ ከስነ ምግባር ጋር የተገናኙ ውሳኔዎችን ወስኗል። የኮሚቴው መደበኛ አባላትም ሆኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት ከአጉል ሰጣ ገባና መገፋፋት ተቆጥበው የቀደመ የህዝባችንን አንድነት የሚገነቡ እና የጋራ አቅማችንን የምናጎለብትበት ስራዎችን በመስራት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። ከማሳሰቢያው በኋላ የሚቀጥሉ የህዝባችንን አንድነት የሚሸረሽሩ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉ አካላት ካሉ በግለሰብ ደረጃ እንጂ የኮሚቴው እንቅስቃሴ እንዳልሆነ ከወዲሁ እያሳወቅን ክትትል እያደረግን የእርማት መንገዶችን እየተከተልን አማራዊ ጨዋነት በተሞላበትና የወከለውን ህዝብ ክብር በሚመጥን መልኩ የተነሳበትን አንኳር ጉዳይ እልባት ለማስገኘት ፅኑ አቋም ይዟል። የደራ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚ አዲስ አበባ ሸዋ ኢትዮጵያ! ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች አሻራ ሚዲያ የአይበገሬዎቹ ልሳን:- Youtube:- https://www.youtube.com/channel/UCPmgFzP2ZPmdGjHxXjigJaw Facebook:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም:- https://t.me/asharamedia24

Source: Link to the Post

Leave a Reply