የ’አብን’ እና የፓርላማ አባሉ ክርስቲያን ታደለ ከታሰረ ከ8 ወራት በኋላ ያመለከሰስ መብታቸው ተነሳ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 5 ቀን 2016  ባካሄደው የ3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 17ኛ  መደበኛ ስብሰባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የሆኑትን የምክር ቤት አባል ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት አንስቷል። በመሆኑን በፍርድ ቤት ክስ እንደሚምሰረትባቸው ይጠበቃል።

ክርስቲያን ታደለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ምርጫ ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ወክለው ተወዳድረው ነበር።

ክርስቲያን የምክር ቤቱ አባል ከሆኑ በኋላ በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው በመንግስት ቁጥጥር ስር እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ሆኖም በአማራ ክልል የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ ባለፈው ሐምሌ ወር በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ላላፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ይገኛሉ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር ሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና በምክር ቤቱ የመንግሥት ወጪ፣ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት ክርስቲያን ታደለ ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን እስከዛሬ ድረስ ያለመከሰስ መብታቸው አልተነሳም ነበር።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ከምክር ቤት አባሉ በፌደራል ፖሊስ አባላት ከቤቱ መወሰድ ማግስት ሐምሌ 29 ቀን 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው “ከትናንት ጀምሮ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ስምሪት የሚሰጡ፣ በተለያየ መንገድ ችግሩን የሚያባብሱ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማድረግ ተጀምሯል” ብለው ነበር። 

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት “ማንኛውም የምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።

ክርስቲያን ታደለ ከመታሰራቸው ከቀናት በፊት በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ “የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራ እና የንፁሃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስባለሁ” ብለው ንግግር ያድረጉ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስልጣናቸው እንዲለቁ መጠየቁ አነጋጋሪ ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም። 

በአሁኑ ሰዓት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባሉ ክርስቲያን ታደለ አዋሽ አርባ አካባቢ በሚገኘው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ከበርካታ “በሽብር ድጋፍ” የተጠረጠሩ ግልሰቦች ጋር የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በ2015 ማለቂያ ባደረገው ጉብኝት በአዲስ አበባ ያለው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ በመጣበቡ እስረⶉቹን ወደ አዋሽ አርባ ማምጣት እንዳስፈለገ የፌደራል ፖሊስ ገልጾለት ነበር። 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የተለያዩ ምክር ቤት አባላት የታሰሩ ሲሆን በቅርቡ የአዲስ አበባ ምክር ቤት እንዲሁም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤቶች እያንዳንዳቸው የአንድ አባል ያለመከሰስ መብት ማንሳታቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ አይዘነጋም።

Source: Link to the Post

Leave a Reply