You are currently viewing የአቶ አቻምን ስቃይ ሳስበው፤ ከመፈናቀል እስከ ኮማንድ ፖስት የእስር ስቅይት- ‹‹ወዴት እንሒድ?›› ያልመለስኩት ጥያቄ!

የአቶ አቻምን ስቃይ ሳስበው፤ ከመፈናቀል እስከ ኮማንድ ፖስት የእስር ስቅይት- ‹‹ወዴት እንሒድ?›› ያልመለስኩት ጥያቄ!

በግንቦት 2005 ዓ.ም. ቻግኒ መናኽሪያ አንድ ሰው ተዋወቅኩ፡፡ አጋጣሚው እንዲህ ነው፤ ከቻግኒ መናኻሪያ ወደ ቡለን ወረዳ ባሮዳና ዶቢ ለመሔድ ነው አውቶቡስ ተራ የገባሁት፡፡ በሰው ብዛት (ሁሉም ተመላሽ ተፈናቃይ ነው) የተነሳ መኪና ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን እንዴት መኪና ማግኘት እንዳለብኝ ጠይቄያለሁ፡፡ ግን ጥያቄው ብዙም መፍትሔ አላመጣልኝም፡፡ መናኻሪያው በር አካባቢ ከዶቢ የተመለሰ ሰው አገኘሁ፡፡ ሰው ሁሉ ወደዚያ ለመሔድ እየተጋፋ ባለበት ሰዐት እርሱ ለምን እንደተመለሰ ጠየቅኩት፡፡ ትውውቃችን እንዲህ ከአቶ አቻም ደምሴ ጋር፡፡
አቶ አቻም በጊዜው በ40ዎቹ መካከል ላይ የሚገመት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም. በወያኔ አጋፋሪነት የብዙ ዐማራዎች ቤትና ንብረት ተዘርፎና ወድሞ ሲፈናቀሉ ከተጠቁ ገበሬዎች መካከል ነው አቶ አቻም፡፡ ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ጎጃም ባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ መሸንቲ የምትባል ትንሽ ከተማ አቅራቢያ ነው፡፡ አቶ አቻም እንደነገረኝ መሸንቲን ከቆረቆሯት ሰዎች መካከል አባቱ ይገኙበታል፡፡
ይህ ሰው ወደ መተከል ከ15 ዓመታት በፊት ነው የሔደው (ልብ አድርጉ ከጎጃም ወደ ጎጃም ነው)፡፡ ሀብት ንብረት ያፈራው ቤተሰብም የመሠረተው እዚሁ መተከል (ጎጃም) ነው፡፡ ዐማራነት ወንጀል በሆነበት አገር የትም ቢኮን ያው በመሆኑ በአንድ ባልታሰበ ዕለት ወደ አንድ ሚሊዮን በር የሚጠጋ ንብቱ ወድሞ አገር ለቆ እንዲወጣ ተደረገ፡፡
አቻም ዶሮ አርቢ ነው- ከ150 በላይ ዶሮዎች ነበሩት፤ አቻም ንብ አናቢ ነው- 27 ዘመናዊ ቀፎ ንቦች ነበሩት፤ አቻም ጠንካራ ገበሬ ነው- ከ3 ሔክታር በላይ ቃሪያና ቲማቲም፣ ከ50 ኩንታል በላይ ዳጉሳና ጤፍ…. ተነግሮ የማያልቅ ጸጋ ባለቤት ነበር፡፡ ይህ ሰው ከብት አርቢም ነበር- አንድ በረት ሙሉ የቀንድ ከብቶች ነበሩት፡፡ 62 ዚንጎ ቆርቆሮ ቤት ከነተሟላ ዕቃው የአቶ አቻም ንብረት ነበር፡፡ ግን ይህ ሁሉ ከመጋቢት 2005 ዓ.ም. በፊት ነው፡፡ አሁን ሁሉም ተረት የተረት ተረት ነው፡፡
በወያኔ ዘመን የዐማራ ሀብት የጠዋት ጤዛ ነው፤ የዐማራ ወጣትነትም አበባ ነው፡፡ አንድ ቀን ባልሞላ ጊዜ ሀብቱ ይረግፋል፤ የወጣትነት ዘመናችን ሳናጣጥመው በጥይት እንለቀማለን ወይ እንታሰራለን፡፡ ይህ ነው የዐማራ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በዚህ ዘመን፡፡
እንግዲህ አቻምን ያወቅኩት ይህን ሁሉ የወደመ ንብረት አይቶ ሲመለስ ነው፡፡ ተስፋው ተሟጦ ጠፍቷል፤ ቅስሙ ተሰብሯል፡፡ ለማጽናናትም ለማስተዛዘንም ከባድ ነው፡፡ በእንዲህ ያለ ጊዜ ከተጎጂው ለአጽናኚው ይከብዳል፡፡
ከዚህ በፊት ይህችን ‹‹Inject people with hope›› የምትል አባባል እወዳት ነበር፡፡ ግን ይህን ሰው ምን ዓይነት ተስፋ ልመግበው እችላለው፡፡ ለካስ ሁሉም ነገር ሁልጊዜ አይሠራም፡፡ የስፋቢስነት (Hopelessness)ና የረዳትአልበኝነት (Helplessness) ስሜቱ ከእሱ ይልቅ በእኔ ላይ ብሶ ነበር፡፡
ይህ ግለሰብ ልጆቹ ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ዘመድ አዝማድ ኬንዳ ዘርግቶለት በመሸንቲ ከተማ መኖር ጀመረ፡፡ ከዚያች ተወልዶ ካደገባት ከተማ ደግሞ መታወቂያ ስለሌለው ምንም ዓይነት ሥራ ከመሥራት ታገደ፡፡ መታወቂያ ለማውጣት ቀድሞ ከነበረበት ቦታ ሒዶ መሸኛ ይዞ መመለስ ነበረበት፡፡ የግድ ነው፤ ሔደ፡፡ በሔደበት ታሰረና ግልገል በለስ ማረሚያ ቤት ገባ፡፡ በቀን ሥራ የእለት ምግባቸውን የሚመግባቸው አራቱ ልጆቹና ሚስቱ ጎዳና ሊወጡ ሆነ፡፡ ባለቤቱ የጉልበት ሥራ ጀመረች፡፡ ከሳምንታት ዕስር በኋላ ያለምንም ክስ እንዲሁ ተፈታ፡፡
ታሪኩ ብቻ ብዙ ነው፡፡ ታሪኩን ለማሳጠር አቻም ባሕር ዳር ጣይቱ መዝናኛ ሆቴል የሌሊት ጥበቃነት ተቀጠረ፡፡ በቀን ደግሞ ከተለያዩ ወገኖች ልገሳ በገኛት ትንሽ ሳንቲም በአነስተኛ ንግድ ሕይወቱን ይመራ ጀመር፡፡……
ከዚህ ሁሉ በኋላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንድ መጥፎ መልዕክት ደረሰኝ፤ አቶ አቻም ደምሴ በኮማንድ ፖስቱ ታስሯል የሚል፡፡ አቶ አቻም ከታሰረ አንድ ወር ይሆነዋል፤ ቤተሰብም እንደፈለገ ስለማይጠይቀው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለም ማወቅ አልቻልኩም፡፡ የሰማሁት ባሕር ዳር እንደታሰረ ነው፡፡
ስለአቶ አቻም መረጃውን የሰጠኝ የብዙ ዘመን ጓደኛው ይህን አለኝ ‹‹ወዴት እንሒድ? መተከል በገንዛ አገራችን ተባረረን! ከአባቶቻችን ቀየ ከታሰርን ወዴት እንሒድ? ምንስ እናድርግ?››
ለዚህ ጥያቄ መልስ ያለው አለ? የአቶ አቻም ጓደኛ ጥያቄ የአንድ ሰው ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ መላው የዐማራ ሕዝብ በወያኔ ዘመን የሚጠይቀው ነው፡፡ መልስ ይሻል፡፡

Muluken Tesfaw

Leave a Reply