የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን በተመለከተ አስቻይ የሕግ እና ተቋማዊ ማእቀፎች ሊቀረጹ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡አካል ጉዳተኞች እና አረጋ…

የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን በተመለከተ አስቻይ የሕግ እና ተቋማዊ ማእቀፎች ሊቀረጹ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡

አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ከተቋማዊ የአሠራር ክፍተቶችና ከተሳሳቱ አመለካከቶች የተነሳ የሚገጥሟቸውን መሰናክሎች ለመቅረፍ ወጥ ተቋማዊ መዋቅር መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ነዉ የገለጸዉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀውን ባለ 44 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ እንደገለጸዉ ይህ ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት በተለይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ላይ በዝርዝር በማተኮር በበጀት ዓመቱ የታዩ መልካም እመርታዎች፣ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ ሐሳቦችን ይዟል።

በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት መረጃዎች እና ማስረጃዎች በዋናነት በኮሚሽኑ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2015 ዓ.ም. ካከናወኗቸው የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሥራዎች፣ በግለሰቦች እና በሲቪክ ማኅበራት የቀረቡ አቤቱታዎች፣ መለስተኛ ጥናቶች እና በልዩ ልዩ የምክክር መድረኮች ላይ የተገኙ ግብአቶችን መሠረት ያደረጉ መሆናቸዉን ገልጿል፡፡

በሪፖርቱ ከተካተቱ ዋና እመርታዎች መካከል የአካል ጉዳተኞች ስምምነትን መሠረት ያደረገ ረቂቅ አዋጅ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡ፣ የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች ፕሮቶኮልን ለማጽደቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ መቅረቡ፣ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ ድርጅት መቋቋሙ እና የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት አካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች የአካል ድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱ ይገኙበታል።

እንደ ተግዳሮት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ፤ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያንን ጉዳዮች የሚመለከተው ተቋማዊ መዋቅር ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ባሉት የመንግሥት መዋቅሮች ወጥ ባለመሆኑ የሚፈጠሩ የአሠራር መዘበራረቆች እና አስተዳደራዊ ቅሬታዎችና በደሎች መበራከታቸው፣ ሀገራዊ ሕግጋትን ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ለማጣጣም የሚደረገው እርምጃ ፈጣን አለመሆኑ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የሚያጋጥሟቸው ዘርፈ-ብዙ ችግሮችይገኙበታል፡፡

ሌላዉ አሳሳቢ ጉዳይ ተብሎ በሪፖርቱ የተነሳዉ በሀገሪቱ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የአካል ጉዳተኞች ቁጥር መጨመሩና የአካል ድጋፍና ተሐድሶ አገልግሎት ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑ እንዲሁም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተቀበሩ ፈንጂዎች እያደረሱት ያለውን የሞትና አካል ጉዳት ሥጋት አሳሳቢነት ነዉ፡፡

በተጨማሪም በመንግሥትም ሆነ በግል የሕፃናት መንከባከቢያ ተቋማት አካል ጉዳትን መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶች በሚፈለገው መጠን አለመኖራቸው፣ ክብረ-ነክ ቃላት (Derogatory Terms) የመሪነት፣ የኃላፊነት እና የአስተማሪነት ሚና ባላቸው ሰዎች በመገናኛ ብዙኃን ጥቅም ላይ መዋላቸው እና የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ትክክለኛ ቁጥር አለመታወቁ አሳሳቢ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፤ ሪፖርቱ ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች በቂ ጥበቃ የሚያደርጉ ሕጎችና ፖሊሲዎች አለመኖር ፣በይዘትና አተገባበር ሂደታቸው ላይ በሚታዩ ክፍተቶች ወይም ከተቋማዊ አሠራሮችና ከተሳሳቱ አመለካከቶች የመነጩ ዐይነተ-ብዙ መሰናክሎችን በዘላቂነት ለማስቀረት ጥሩ ግብአት እንደሚሆን ተናግረዋል።

በሪፖርቱ የተካተቱ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉም ኮሚሽነሯ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በእስከዳር ግርማ

ጳጉሜ 02 ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube
https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/video

Source: Link to the Post

Leave a Reply