የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በወሎ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦር 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰንጋ ድጋፍ አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም…

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በወሎ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦር 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰንጋ ድጋፍ አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል ህዳር 6 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በወሎ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦር 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሰንጋ በመካነ ሰላም ከተማ ተገኝቶ ድጋፍ አድርጓል። በግንባሩ የአገው ፈረሰኞች ማኅበርም ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉን ያስረከቡት የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ በላይነህ የኔሰው ብሔረሰብ አስተዳደሩ በሦስት ግንባሮች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። ብሔረሰብ አስተዳደሩ በማይጠብሪ እና በወሎ ግንባር ለሚገኘው የወገን ጦር ድጋፍ አድርጓል። በመተከል ዞን ሰላም እያስከበረ ለሚገኘው የወገን ጦርም ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ ሰፊ የማኅበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር የሀብት ማሰባሰብ ሥራ መሥራታቸውንም ነው የገለጹት። በወሎ ግንባር 116 ሰንጋዎችን ፣ 118 ፍየሎች እና 15 በጎች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል። በወሎ ግንባር የተደረገው ድጋፍ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት መሆኑንም አስታውቀዋል። በብሔረሰብ አስተዳደሩ በተለያዩ ግንባሮች የተላከው ድጋፍ ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ገልጸዋል። ብሔረሰብ አስተዳደሩ ለሦስተኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉንም አመላክተዋል። ድጋፉ በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም ብለዋል። ብሔረሰብ አስተዳደሩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሚሊሻና ወጣቶችን ለዘመቻ መላኩንም አስታውቀዋል። የገባው ዘማችም ጀብዱ እየፈጸመ መሆኑን ነው ያነሱት። የጠላት ግብዓተ መሬት እስኪፈጸም የሚደረገው ኹሉን አቀፍ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ በላይነህ የብሔረሰብ አስተዳደሩ እናቶች ያለማቋረጥ ለሠራዊቱ ሥንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ሰብሳቢ ጥላዬ አየነው የፈረሰኛ ማኅበሩ ለሕልውና ዘመቻው የሚጠበቅበትን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል። አባቶች በፈረስ ተጉዘው በጦርና በጎራዴ ኢትዮጵያን ከጠላት ወረራ ነፃ እንዳወጧት የገለፁት ሰብሳቢው ከቅኝ ተገዢነት ነፃ አውጥተው ለቀጣይ ትውልድ አስረክበዋል፤ አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የአባቶቹን ፈለግ ተከትሎ የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ ጠይቀዋል። ማኅበሩ 600 ሺህ ብር በማሰባሰብ 120 በጎችን ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል። የፈረስኞች ማኅበሩ የስንቅ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ እንደ ጀግኖች አባቶቹ በውጊያ ለመሳተፍ ቁርጠኛ መሆኑንም አስታውቀዋል። አባሉ ለመዝመት ዝግጁ እንደሆነም ነው የጠቆሙት። ድጋፉን የተቀበሉት በግንባሩ የአማራ ልዩ ኅይል የሎጅስቲክ አስተባባሪ ሻለቃ አማረ ተሰማ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በተደጋጋሚ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል። የተደረገው ድጋፍ ለሠራዊቱ ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሚሆነውም ተናግረዋል። ሠራዊቱ ለሚኖረው ግዳጅ የሕዝቡ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አለውም ነው ያሉት። ዘገባውየአሚኮ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply