የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፍ ገለጸ

ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአውሮፓ የውጭ ጉዳይ አገልግሎት የአፍሪካ ጉዳይ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂንሃን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ኹኔታ እና የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ስላደረገው የሰላም ግንባታ ጥረት ገለጻ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ሕብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው፣ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሪታ ላርንጃንሃ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጂካዊ አጋርነቱን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፍ ገልፀው፤ ይህን ለማገዝ የአውሮፓ ህብረት የሰላም ሂደቱን በሚፈለገው ጊዜ ለመርዳት ያለውን ፍላጎት አጽንኦት መሰጠቱን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply