የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚፈጠረውን አደጋ ለመከላከል ድጋፍ ያደርጋል – ባለስልጣናቱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚፈጠረውን አደጋ ለመከላከል የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ የህብረቱ የግጭት አስተዳደር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺች ገለጹ።

የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በዘላቂነት ወደ መኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱና የበረሃ አንበጣን ጉዳት ለመከለከል ድጋፍ ያደርጋልም ተብሏል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል የሚመራ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርጓል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ውይይት ከማድረግም ባለፈ፤ በሶማሌ ክልል የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያን ጎብኝተዋል።

የህብረቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በተመለከተም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የህብረቱ የግጭት አስተዳደር ኮሚሽነር ጄንዝ ሌናርሲክ እንዳሉት በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ አደጋዎች ይከሰታሉ።

የበረሀ አንበጣ መንጋ፣ ድርቅ፣ ኮቪድ-19 ፣ ግጭት በአፍሪካ ምድር በተደጋጋሚ እየተከሰቱ አፍሪካውያንን ለችግር ሲያጋልጡ ይታያል ብለዋል።

በመሆኑም ህብረቱ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ የተከሰተው ችግር ለመከላከል አስቸኳይ እርዳታ ከማድረግ ባለፈ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

የህብረቱ የውጭ ጉዳይና ደኅንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይና ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየትኛውም አገር ለውጥ ሲመጣ ፍርሃትን በመፍጠር እስከ ግጭት የመድረስ ባህርይ እንዳለውም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነት እንዲኖረውና ሰላም እንዲሰፍን ሁሉን አቀፍ አገራዊ ውይይት ማድረግ ይገባል ሲሉ ነው የተናገሩት።

ህብረቱም ለውጡን በመደገፍ ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድና መረጋጋት እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

ኮሚሽነር ሌናርቺች ልዑኩ በሶማሌ ክልል የተፈናቃዮችን መጠለያ መጎብኘቱንና ህብረቱ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እያደረገ መሆኑኑንም ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች በራሳቸው ፍላጎት፣ ደህንነታቸው ተጠብቆ በዘላቂነት ወደመኖሪያ ቀያቸው እንዲመለሱ ከአካባቢው ተወካዮች ጋር ተወያይተናል፤ ድጋፍም እናደርጋለን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

The post የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚፈጠረውን አደጋ ለመከላከል ድጋፍ ያደርጋል – ባለስልጣናቱ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply