የአውሮፕላን ድብደባዉ በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተወሰደ እርምጃ ነዉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17፣ 2013 ሰሞኑን የሚነዛው የአውሮፕላን ድብደባ በተመረጠ መልኩ በአሸባሪው ህወሓት ላይ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ገለፀ:: የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሰጡት መግለጫ፤ህዝቡን በውሸት በማደናገር አሽንፈናል በማለት ማጭበርበር ዋና ተግባሩ የሆነው ይህ አሸባሪ ቡድን፤ ሰሞኑን የሚነዛው የአውሮፕላን ድብደባም እሱ እንደሚለው ሳይሆን ሰኔ 15 ቀን የሰማእታት ቀንን እናከብራለን በሚል ከተደበቀበት በወጣበት ወቅት በተመረጠ መልኩ በራሱ ላይ ብቻ የተወሰደ እርምጃ ነዉ ብለዋል የቡድኑ ርዝራዥም የትግራይን ህዝብ ሰላማዊ ኑሮ እየረበሸ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለህግ ማስከበር ዘመቻው በትግራይ ተሰማርቶ የነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለምርጫው ሰላማዊነት ሲባል ወደሌላ የሀገሪቱ አካባቢዎች መንቀሳቀሱን ተከትሎ የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዥ ሚሊሻዎች ከተደበቁበት ጢሻ በመውጣት ሰላማዊውን የትግራይ ህዝብ ሲያሸብሩ ነበር ተብሏል፡፡ ሀገራዊ ምርጫውን ተከትሎ ከውጭም ከውስጥም ስጋት ስለነበር ሰራዊቱ በመንግስት ትዕዛዝ መሰረት ከትግራይ ወደ ማዕከል፣ ምስራቅ፣ ምእራብና የደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል።

ይህን ሁኔታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በየጢሻው ተደብቆ የነበረው የአሸባሪው ህወሓት ሚሊሻ ህዝቡን ሲያስገድድና ሰላማዊ እንቅስቃሴውን ሲያስተጓጉል ነበር ብሏል። መከላከያ ሰራዊቱ በወሰደው እርምጃ ህዝብን ወደ ሰላማዊ ኑሮው መመለስ መቻሉም በመግለጫዉ ተገልጿል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት በመስራት ገበሬው እንዲያርስ፣ ነጋዴው እንዲነግድ፣ ተማሪዎች እንዲማሩ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩ መገለጹን ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply