የአይ ኤም ኤፍ መደራደሪያ ሀሳብ በኢትዮጵያ ያለውን የዋጋ ግሽበት ሊያባብሰው እንደሚችል ተነገረ፡፡

በቅርቡ አይ ኤም ኤፍ |IMF| እና ኢትዮጵያ በብድር እና መሰል ሁኔታዎች ዙሪያ ውይይት ማካሄዳቸው ይታወቃል።

በአዲስ አበባ በነበረው ውይይቱ ከስምምነት ሳይደርሱ መለያየታቸው የተለያዩ ምንጮች መዘገባቸው የሚታወስ ነው።

አይ ኤም ኤፍም ኢትዮጵያ ብድሩን ለማግኘት እንድተችል የተለያዩ አሰግዳጅ የፖሊሲ ቅድመ ሁኔታዎች እያስቀመጠ እንደነበር ተዘግቧል።

ሬውተርስ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ነግረውኛል ብሎ በሰራው ዘገባ አበዳሪው የገንዘብ ተቋም ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር በነበረው የመጨረሻው ውይይት ወቅት አገሪቱ የገንዘብን የመግዛት አቅም እንድታዳክም በግልጽ ባይጠይቅም፣ የሚለቀቀው ብድር ያንን ማድረግ የሚጠይቅ ነው ሲል ገልጿል።

በዚህም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እያመነቱ የቆዩበትን ብርን ከዶላር ምንዛሬ አንጻር የማዳከም ውሳኔ ምናልባትም ካቀዱት ጊዜ ቀድመው ሊያሳልፉ ይችላሉ ሲል ሬውተርስ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ከዚህ ጋር አያይዘው ሀሳባቸውን ለጣቢያችን የሰጡን የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎችም ብድር ለማግኘት ተብሎ የሚወሰዱ እርምጃዎች ሀገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሞያው አቶ መቆያ ከበደ እንደሚሉትም፤ የአይ ኤም ኤፍ ጥያቄ የገንዘብ የመግዛት ዋጋን እንዲቀንስ የሚያደርግ ከሆነ የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብሰው ስለሚችል በጥንቃቄ መደረግ እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

ምንዛሬው በገበያ ይወሰን የሚለው ሃሳብ መንግስት አያደርገውም የሚሉት አቶ መቆያ ከበደ ንግዱ በገበያ ከሆነ ቆይቷል ከባንክ አሰራር ካለው ውጪ የእቃ ግብይቱ በጥቁር ገብያው ጋር ተመሳሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሞያው ዶ/ር አጥላው አለሙ በበኩላቸው፤ ገንዘብን የማዳከም አንዲሁም የፕራይቬታይዜሽን ጉዳይ የአይ ኤም ኤፍ አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደሆኑ በማነሳት የሚደረገው ውይይት ጥቅም አልባ እና መንግስት የተባለውን ቢቀበለም ብድር ይለቀቃል ስፊው ማህበረሰብን ግን በተባባሰ የዋጋ ግሽበት ውስጥ እንደሚኖር ተናግረዋል።

ገንዘብን ማዳከም እና የዋጋ ንረት ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳላቸው የሚናገሩት ሌላኛው የምጣኔ ሃበት ባለሞያው አቶ ጌታቸው አስፋው መንግስት የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ውሳኔ ከወሰነ የዋጋ ንረቱም በዛው ልክ ከፍ እንደሚል አንስተው የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር ስለሚችል ገንዘብን እንዲዳከም ማድረግ ብዙም አይመከርም ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

በለዓለም አሰፋ

ሚያዝያ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply