የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ምትኩ ካሳ እና ልጃቸው እያሱ ምትኩ ፍርድ ቤት ቀረቡ

👉ፍርድ ቤቱ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል

ሐሙስ ሐምሌ 7 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ከልጃቸው እያሱ ምትኩ ጋር በተጠረጠሩበት የሙስና እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም ወንጀል በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎችን በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያቀረበው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪዎች፤ ምትኩ ካሳ የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ሲሰሩ ከኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመመሳጠር የተረጂዎችን ቁጥር ከፍ በማድረግና የሌሉ ተረጂዎችን እንዳሉ በማስመሰል አገሪቱ በከፍተኛ በውጭ ምንዛሬ ያስገባችውን የገንዘብ ግምቱ በሚሊዮኖች የሚገመት ከ700 ሺህ 200 ኩንታል በላይ የስንዴና ቦቆሎ እህል እንዲሁም 208 ሺህ ሊትር የዘይት እና ጥሬ ገንዘብ ከሚመሩት ተቋም በሳቸው ፍቃድ ወጪ ተደርጎ ለኤልሻዳይ ድርጅት መሰጠቱን ጠቁሟል።

በኹለተኛ ተጠርጣሪ በልጃቸው እያሱ ምትኩ ሥም ከኤልሻዳይ ድርጅት የተገዙለት ኹለት መኪኖች መኖራቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ በተጨማሪ ኤልሻዳይ ከ2013 ጀምሮ ለልጃቸው በወር 15 ሺህ ብር የቤት ኪራይ ተከራይቶለት እንደሚኖር ፖሊስ ጠቁሟል።

እንደአጠቃላይ በጎዳና ያሉ ዜጎችን ለማሰልጠን በሚል ለኤልሻዳይ ከ2006 እስከ 2012 ባሉት ጊዜያት 472 ሚሊዮን 886 ሺህ 304.33 ብር ወጪ ተደርጎ ድርጅቱ ተከፋይ መሆኑን ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ያልተገባ ጥቅም በማግኘት ቤትና የተለያዩ ንብረት ማፍራታቸውን ጠቅሶ ምንጩ ያልታወቀ የውጭ አገር ገንዘብ መገኘቱንም አመላክቷል።

“አገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ላይ መሆኗ እየታወቀ የተለያዩ የውጭ አገር ገንዘብ አከማችተው መገኘቱን ተከትሎ ምንጩን እያጣራን ነው” ብሏል ፖሊስ በሪፖርቱ።

15 ምስክር ቃልና በርካታ አስረጂ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡን ገልጾ፤ ለቀሪ 10 ምስክር ቃል ለመቀበል እና ግብረ አበር ለመያዝ ቀሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ፈትሉ ኑሬና እና ሀብተማርያም ፀጋዬ በበኩላቸው፤ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ፖሊስ ምርመራ አጠናቆ ኦዲት ተደርጎ በቂ ማስረጃ መሰብሰቡን በመግለጫ በሚዲያ ባሳወቀበት ኹኔታ ዛሬ ደግሞ ማስረጃ ለመሰብሰብ 14 ቀን ይሰጠኝ ማለቱ አሳማኝ ያልሆነና ተገቢነት የሌለው ጥያቄ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

በሌላ በኩል ምትኩ የተረጂዎችን ቁጥር መጨመርና የሌሉትን እንዳሉ በማድረግ የመመዝገብና የማሳወቅ ሀላፊነት የለባቸውም ሲሉ አሰረድተዋል።

እርዳታውንም በተመለከተ ገንዘብ ሚኒስቴር ሲፈቅድ እንጂ በሳቸው ሀላፊነት ፍቃድ የሚሰጥ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ከመንግስት ተቋም የሚሰበሰብ ማስረጃን ማጥፋት ስለማይችሉ በዋስ ወጥተው ምርመራው እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በጠበቆቹ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄም ፖሊስ ተቃውሟል።

ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ፤ ከጉዳዩ ውስብስብነት አንጻር ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊነቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለፖሊስ የ 14 ቀን ጊዜ መፍቀዱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ዘግባለች።

Source: Link to the Post

Leave a Reply