You are currently viewing የአዲስ አበባ መስተዳድር ለበላይ አመራርሮች አዲስ  የጥቅማ ጥቅም ድጎማ አዘጋጀ

የአዲስ አበባ መስተዳድር ለበላይ አመራርሮች አዲስ  የጥቅማ ጥቅም ድጎማ አዘጋጀ

Mayor Adanech Abiebe

ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማው ለሚገኙ የተለያዩ ተቋማት አመራሮች አዲስ የጥቅማ ጥቅም መመሪያ ማጽደቁን ዋዜማ ሰምታለች።

መመሪያው በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ቢሮዎች ፣ኤጀንሲዎች ፣ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ውስጥ ያሉ አመራሮችን የሚያጠቃልል መሆኑንም ሰምተናል።

የጥቅማ ጥቅም መመሪያው ከታክስ ነጻ የሆነ ክፍያን፣ ቤት ለሌላቸው አመራሮች ቤት መስጠትን እንዲሁም ቤት ላላቸው አመራሮች የቤት እድሳት ወጪን መሸፈን  እንዲሁም የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማቅረብን ያካትታል። ሆኖም የጥቅማ ጥቅም መመሪያ ከአመራር ውጭ ያሉ የበታች ፈጻሚዎችን እንደማይመለከትም ተረድተናል።

በብር ተሰልቶ የሚከፈለውና ከታክስ ውጭ ሆኖ በተለያየ እርከን ላሉ አመራርች የሚሰጠው ጥቅማ ጥቅም ከፍተኛው 15 ሺህ 200 ብር ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ 5 ሺህ 800 ብር ነው።

ከዚህ ቀደም ለአመራሮች በጥሬ ገንዘብ የሚሰጠው ከፍተኛው ድጎማ ስምንት ሺህ ብር አካባቢ ሲሆን ዝቅተኛው ደግሞ ሁለት ሺህ ብር ገደማ ነበር። በጥሬ ገንዘብ ይሰጥ የነበረው ጥቅማ ጥቅም አሁን ላይ በእጥፍ አድጓል።

ለአመራሮች እንዲሰጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጸደቀው መመሪያ ውስጥ የተካተቱት የማይመለሱ ላፕቶፕ ኮምፒውተር ፣ ሞባይል ስልክ እዲሁም የቤት እድሳት ወጪዎች ይገኙበታል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ አስራ አንድ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ካሉ አመራሮች ፣ ከክፍለ ከተማው ስራ አስፈጻሚ እስከ ቡድን መሪ ድረስ ያሉት አመራሮች እንዲሁም በየክፍለ ከተማው ያሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አመራሮች የጥቅማ ጥቅም በመመሪያው መስረት ተጠቃሚ ይሆናሉ።

በከተማው ባሉት ሁሉም ወረዳዎች ያሉ የወረዳ ስራ አስፈጻሚ እና ምክትል ስራ አስጻሚዎች እንዲሁም የየወረዳው ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሀላፊዎችን ጨምሮ በጥቅሉ ከየወረዳው አምስት አምስት ሰዎች የጥቅማ ጥቅም መመሪያው እንደሚያካትታቸው ተረድተናል።

በከተማ አስተዳደሩ ስር ያሉ ቢሮዎች እና ኤጀንሲዎች ላሉ አመራሮችም እንዲሁ በተመሳሳይ መመሪያው የሚተገበር ይሆናል።  በዚህም የየተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከደሞዙ ውጭ በጥሬ ብር በየወሩ 15, 200 ብር የሚያገኝ ሲሆን በተዋረድ ዝቅተኛ የአመራር እርከን ላይ ያሉት ደግሞ 5,800 ብር የሚያገኙ ይሆናል።

ሆኖም የጥቅማ ጥቅም መመሪያው በከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ያሉ ከአመራር ውጭ ያሉ ሰራተኞችን የሚመለከት አይደለም። [ዋዜማ]

The post የአዲስ አበባ መስተዳድር ለበላይ አመራርሮች አዲስ  የጥቅማ ጥቅም ድጎማ አዘጋጀ first appeared on Wazemaradio.

The post የአዲስ አበባ መስተዳድር ለበላይ አመራርሮች አዲስ  የጥቅማ ጥቅም ድጎማ አዘጋጀ appeared first on Wazemaradio.

Source: Link to the Post

Leave a Reply