You are currently viewing የአዲስ አበባ አምስት ክፍለ ከተሞች፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለታሰሩ ሰዎች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

የአዲስ አበባ አምስት ክፍለ ከተሞች፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለታሰሩ ሰዎች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከተማ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ለመከታተል በናሙናነት ከመረጣቸው ክፍለ ከተሞች ውስጥ መረጃ ያገኘው ከሁለቱ ብቻ መሆኑን አስታወቀ። የክትትል ቡድን ባሰማራባቸው የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ አካባቢዎች ወደ አንድ ሺህ ገደማ ሰዎች መታሰራቸውን ማረጋገጡን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ የታሳሪዎች ቁጥር ከዚህ በላይም ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል።

የኢሰመኮ የክትትል እና ምርመራ የስራ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 11 ክፍለ ከተሞች ውስጥ ለናሙናነት የመረጣቸው ሰባት ክፍለ ከተሞችን ነበር። ከሰባቱ ክፍለ ከተሞች ውስጥ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ የሆኑት በቂርቆስ እና የካ ክፍለ ከተሞች ያሉ አመራሮች ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል። 

ኢሰመኮ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 8፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ ለኮሚሽኑ መረጃ ለመስጠት “አሻፈረን” ያሉት የአዲስ ከተማ፣ ልደታ፣ ጉለሌ፣ ቦሌ እና አራዳ ክፍለ ከተሞች መሆናቸውን አድርጓል። የአምስቱ ክፍለ ከተማዎች ኃላፊዎች “ከበላይ ትዕዛዝ ካልመጣ መረጃ አንሰጥም፣ እስረኛም መጎብኘት አትችሉም” ማለታቸውን ጨምሮ ጠቅሷል።

የኃላፊዎቹ ክልከላ ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት እንዳይወጣ ምክንያት እንደሆነበት አጽንኦት ሰጥቷል። መረጃ ከለከሉ የተባሉትን ኃላፊዎችን ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ “የነገሩን እውነተኛነት እያጣራን ነው” ሲሉ አሁን በጉዳዩ ላይ ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን አያያዝ እና የታሳሪዎችን ሁኔታ ለመከታተል በሚያስችለው መልኩ መረጃ ማሰባሰብ አለመቻሉ እንደሚያሳስበው በዛሬው መግለጫው አስታውቋል።  “በኮሚሽኑ ክትትል የታሰሩ ሰዎችን ብዛት በሚመለከት የተሟላ መረጃ ለማግኘት አልተቻለም” ያለው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ  ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደታሰሩ እንደሚገመት ገልጿል። 

ኮሚሽኑ ለዚህ ግምቱ መነሻ ያደረገው “በአንጻራዊነት የተሟላ መረጃ አግኝቼበታለሁ” ባለው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ እንዲሁም በድሬዳዋ የተገኘ አሃዝን ነው። በአዲስ አበባ በየክፍለ ከተሞቹ ተመሳሳይ እስሮች መከናወናቸውን እና ሰዎችን በቁጥጥር ስር የመዋሉ ሂደት አሁንም መቀጠሉ፤ ኮሚሽኑ ካረጋገጠው ውጭ የታሳሪዎችን ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁሟል።      

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ እስከ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ህዳር 2፤ 2014 ድረስ 714 ሰዎች መታሰራቸውን ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል። ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ ኮሚሽኑ የክትትል ቡድን ባሰማራበት በድሬዳዋ ከተማም 300 ሰዎች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን አስታውቋል። በዚህም መሰረት እስካሁን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ፤ በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ብቻ 1,014 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።  

በአዲስ አበባው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ 241 ሰዎች ታስረው የሚገኙት፤ ስፋቱ 20 ሜትር በ10 ሜትር በሆነ ሁለገብ አዳራሽ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል። ከታሳሪዎቹ ውስጥ አረጋውያንን እና የአዕምሮ ህሙማን እንደሚገኙበት አመልክቷል። በዚህ የማቆያ ስፍራ ያሉ ታሳሪዎች “በግቢው ያለውን ብቸኛ መጸዳጃ ቤት ለመጋራት ተገድደዋል” ብሏል ኮሚሽኑ። 

በአንዳንድ ጣቢያዎች ደግሞ ሴቶች እና ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ ተቀላቅለው መታሰራቸውንም ኢሰመኮ አመልክቷል። ኮሚሽኑ “አንዳንድ ጣቢያዎች እና የማቆያ ስፍራዎች በጣም የተጣበቡ፣ በቂ መጸዳጃ የሌላቸው፤ በቂ አየር እና ብርሃን የማያገኙ ናቸው” ሲል የተመለከታቸው የማቆያ ስፍራዎች ምን እንደሚመስሉ በመግለጫው አብራርቷል። 

በማቆያ ስፍራዎች ያለው የታሳሪዎች የጤና ሁኔታ እና የጤና አገልግሎት ለሌላው በኮሚሽኑ መግለጫ የተነሳ ጉዳይ ነው። ኮሚሽኑ በማቆያ ስፍራዎች ባደረገው ጉብኝት ታሳሪዎች የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት አለመዘርጋቱን እና በህመም ላይ ያሉ ታሳሪዎችን መኖራቸውን ጠቁሟል። ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘም በማቆያ ስፍራዎች “ምንም ዓይነት የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ ጥንቃቄዎች አይደረጉም” ሲል ታሳሪዎች ያሉበትን አስጊ ሁኔታ በመግለጫው አንስቷል።

በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች አረጋውያን እና ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከእስር ከተለቀቁ በኋላ “የተለቀቃችሁት ከኮማንድ ፖስት እውቅና ውጭ ነው” በሚል እንደገና መታሰራቸውን አስታውቋል። የተለቀቁ ሰዎች ድጋሜ ለእስር የተዳረጉት “ከእስር የመፍታት እና የማጣራት ሂደቱ ወጥ ባለመሆኑ” ነው ብሏል። 

ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ “ሰዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ” እየታሰሩ መሆኑን የጠቀሰው ኢሰመኮ፤ በዛሬው መግለጫው ተጠርጣሪዎች የሚታሰሩበትን መንገድም ተችቷል። ተጠርጣሪዎች ከህብረተሰቡ ተገኘ በተባለ ጥቆማ እንደሚታሰሩ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ “የጥቆማዎቹ መነሻ የሰዎቹ የብሔር ማንነት አለመሆኑን ለማረጋገጥ በቂ ጥረት እየተደረገ አይደለም” ሲል ነቅፏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የትግራይ ተወላጅ አለመሆናቸውን በማሳየት ከእስር ሲፈቱ የኮሚሽኑ ባለሙያዎች መመልከታቸውን ጨምሮ ገልጿል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ታሳሪዎችም “የተያዙት በብሔራቸው ምክንያት እንደሆነ እንደሚያምኑ እና የተጠረጠሩበትንና የተያዙበት ምክንያት እንዳልተነገራቸው” ማስረዳታቸውን በመግለጫው አብራርቷል። ከአዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ከዋሉ ተጠርጣሪዎች ውስጥ “የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ሰዎች ብዛት ከፍተኛ መሆኑን” ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል። 

ብሔር ተኮር እስር ተከናውኗል መባሉን በተመለከተ ኢሰመኮ የህግ አስከባሪ አካላትን መጠየቁን በመግለጫው ጠቅሷል። “በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሁለቱም ድርጅቶች ብሔር ተኮር ድርጅቶች ከመሆናቸው አኳያ የሚያዙ ሰዎች የአንድ ብሔር ሊመስሉ ይችላሉ” የሚል ምላሽ ማግኘቱን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ባለፈው ወር ጥቅምት 25 በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው፤ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ለማድረግ” ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ ስልጣን ሰጥቶታል። ኢሰመኮ በዛሬ መግለጫው፤ ሰዎችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሂደት “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ መሆን የሚሉትን የሰብአዊ መብት መርሆዎችን ባከበረ መልኩ አለመተግበሩን” አጽንኦት ሰጥቶ አንስቷል። 

ኮሚሽኑ በመግለጫው ማጠቃለያ ምክንያታዊ ጥርጣሬ መኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ ያልተገኘባቸውን ሰዎች፣ አረጋውያንን፣ የሚያጠቡ እናቶችን እና የጤና እክል ያለባቸውን ሰዎች “በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ” ጥሪ አቅርቧል። የተያዙ ሰዎች ሰብዓዊ አያያዝ እንዲሻሻል ያሳሰበው የኮሚሽኑ መግለጫ “የሚያዙ ሰዎች ሁሉ የታሰሩት በምክንያታዊ ጥርጣሬ መሆኑን” የህግ አስከባሪዎች እንዲያረጋግጡ ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

The post የአዲስ አበባ አምስት ክፍለ ከተሞች፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለታሰሩ ሰዎች መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ኢሰመኮ አስታወቀ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply