ሐሙስ ግንቦት 3 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት የ2015 ትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ቀን እንዲስተካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮን ጠይቋል።
ምክር ቤቱ ለከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ፤ የ2015 ትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ሰኔ 19 እና 20/2015 ለመስጠት ማቀዱን ለመረዳት መቻሉን ገልጿል።
ነገር ግን ”በካላንደር ዝግ የሆኑ የህዝብ በዓላትን ባገናዘበ መልኩ እቅድ ማዘጋጀት የቢሮዉ ሃላፊነት ቢሆንም ሰኔ 20 እና 21 2015 የሚከበሩት የአረፋ እና የኢድ አል-አድሃ በዓል ቀን እና ዋዜማ ፈተና ለመስጠት ማቀድ አግባብነት የሌለዉ እና ተማሪዎች ተረጋግተዉ ፈተና ላይ እንዳይቀመጡ የሚያደርግ ተግባር ነዉ።“ ሲል ገልጿል።
በመሆኑም የፈተናዉን ቀን ከኢድ አል-አደሓ በዓል 3 ቀን በፊት ወይም 3 ቀን በኋላ እንዲሆን እና ይህም በአንድ ሳምንት ጊዜ ዉስጥ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ምክር ቤቱ በደብዳቤው ጠይቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የ 6ኛ እና 8 ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ቀናት ግንቦት 1/2015 ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም የ 8ኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 19 እና 20 እንዲሁም፤ የ 6ኛ ክፍል ፈተና ሰኔ 26 እና 27 እንደሚሰጥ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።
The post የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት የከተማ አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና ቀን እንዲስተካከል ጠየቀ first appeared on Addis Maleda.
Source: Link to the Post