የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ፤ ወረዳዎች በከተማዋ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የነበራቸው ሥልጣን ላይ ገደብ አስቀመጠ።

በአዲሱ አሠራር መሠረት ወረዳዎች በራሳቸው ውሳኔ የንግድ ቦታዎችን ማሸግ የሚችሉት ከንግድ ፈቃድ ጋር በተያያዙ ሁለት ጥሰቶች ተፈፅመው ሲያገኙ ብቻ እንደሆነ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ይህን አሠራር ያስተዋወቀው አዲስ ባወጣው “በመንደር የንግድ ቁጥጥር የአሠራር ሥርዓት መመሪያ” ላይ ነው።

መመሪያው፤ የከተማዋ ንግድ ቢሮ፣ ክፍለ ከተሞች ወይም የወረዳ ጽህፈት ቤቶች በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች አሠራር ላይ የሚያደርጉትን የቁጥጥር ሥራ ተፈጻሚነት ያለው እንደሆነ አስፍሯል።

ባለፈው ሳምንት በፍትህ ሚኒስቴር የምዝገባ ሂደቱን ያጠናቀቀው ይህ መመሪያ የወጣው፤ በከተማዋ በነጋዴዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎችን “ፍትሐዊነትን” በተመለከተ “አልፎ አልፎ የሚነሱ ችግሮች” በመኖራቸው እንደሆነ የንግድ ቢሮ የንግድ ክትትል እና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ቅድስት ስጦታው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በተለይ ከእርምጃ አወሳሰድ ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ እና ጤናማ ሂደቱን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ እዚህም እዚያም የሚታዩ ችግሮች አሉ። ‘አላግባብ ታሸገብን፣ አላግባብ ተከፈተ’ የሚሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ” ሲሉ ቢሮው ከእርምጃ አወሳሰድ ጋር በተያያዘ ቢሮው የተመለከታቸውን ችግሮች አብራርተዋል።

የንግድ ቦታዎችን ካሸጉ በኋላ ለማስከፈት የገንዘብ ድርድር ማድረግም ቢሮው “የሥነ ምግባር ብልሽት” ባለባቸው “ውስን ሠራተኞች” ላይ የተመለከተው እና መመሪያው ለመውጣቱ አንዱ መነሻ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ አክለዋል።

ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply