የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የዘርፉ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች እና ታዋቂ የጥበብ ሰዎች ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡ቢሮው “ነገ…

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የዘርፉ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች እና ታዋቂ የጥበብ ሰዎች ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡

ቢሮው “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሀሣብ ነው የችግኝ ተከላ መርሃግበሩን ከዘርፉ የሚዲያ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች ጋር ያከናወነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀንበር ባስተላለፉት መልዕክት “ከተማችንን ብሎም ኢትዮጵያን በአረንጓዴ ልማት የማልበስ ተግባራችን ተጠናክሮ ቀጥሏል ፤ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ እንደ ሃገር ሃላፊነትን ከመወጣት ባሻገር ለቀጣዩ ትውልድ ምቹ ሃገርን ለማስረከብ የሚያስችል እንቅስቃሴ መሆኑን መግለጻቸውን የኤ ኤም ኤን ዘገባ ያመለክታል፡፡

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግርና የእንኳ ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ኮሙንኬሽን ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ እናትዐለም መለሰ “ትናንት በተከናወነው የችግኝ ተከላ ቢሮው በላቀ አስተባባሪነት 10ሺህ ችግኞችን እንደተከለ ጠቁመው በከተማ ደረጃ ያቀድነውን እናሳካለን ብለዋል።

በነገው እለት ሓምሌ 10 በመላው ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኞች ይተከላሉ ተብሎ እቅድ የተያዘ ሲሆን ለዚህም ስኬት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎቿን በነቂስ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በተያያዘ ዜና

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን አስመልክተው በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

“ታሪክ የመቀየር ጉዳይ ነው። ለትውልድ የመትረፍ ጉዳይ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

ከማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ተግባራት ነጻ የሆነ ቀን የመረጥነው ይህ ቀን ሊያልፈው የሚገባ ኢትዮጵያዊ ስለሌለ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ ሰኞን ስንመርጥ የሥራ መጀመሪያችንን ተፈጥሮን በመታደግ እንድንጀምር ነው” ብለዋል።

“ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ነው። ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እና መንደሮች ከአምናው የበለጠ በመትከል የየራሳቸውን ሪከርድ እንደሚሰብሩ እናምናለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

“እያንዳንዳችንም የየራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም፤ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው”ሲሉ ገልጸዋል።

ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን ፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን፤ በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

“ነገ ሐምሌ 10 ቀን 2015 የራሳችሁን ሪከርድ በብዙ መጠን እስክትሰባብሩ ድረስ ዛፎችን ለመትከል ተዘጋጁ ”ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያም

ሐምሌ 09 ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube

https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos

Source: Link to the Post

Leave a Reply