የአዲስ አበባ ወጣቶች በ126ኛው አድዋ ክብረ በዓል ሳቢያ እየታደኑና እየታሰሩ መሆኑን ባልደራስ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ…

የአዲስ አበባ ወጣቶች በ126ኛው አድዋ ክብረ በዓል ሳቢያ እየታደኑና እየታሰሩ መሆኑን ባልደራስ አስታወቀ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 27 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ 126ኛው የአድዋ በዓል ላይ “የተቃውሞ ድምጽ አሰምታችኋል” በሚል የአዲስ አበባ ወጣቶች በፖሊስ እየታደኑና እየታሰሩ ናቸው፡፡ ከተያዙት ወጣቶች መካከል ደረጄ ይበይን፣ አስጨናቂ ተስፋዬ እና ኢዮብ ፍቅሩ ይገኙበታል፡፡ ሌሎች በርካታ ወጣቶች ቢኖሩም፣ ታስረው በሚገኙበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጥየቃ ስለተከለከለ ሙሉ የስም ዝርዝራቸውን ለጊዜው ማግኘት አልቻልንም፡፡ ሙሉውን ዝርዝር እንደደረሰን እናወጣለን። ትላንት ከታሰሩት 33 ባልደራስ አባላት መካከል ቢኒያም ታደሰ እና ሳሙኤል ዲሚትሪ ከ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወስደዋል፡፡ ምክንያቱ ባይታወቅም፣ ሲቪል የለበሱ የፖሊስ ወይም የደህንነት አባላት፣ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኙት የባልደራስ አባላት እስር ቤት ዘልቀው በመግባት፣ “ቢኒያም እና ሳሙኤል የት ናቸው?” ብለው ጠይቀዋል፡፡ የአድዋ የድል በዓል በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ መስተዳድር ባወጣው መግለጫ ያረጋገጠው ሐቅ በመሆኑ፣ በወቅቱ ሃሳባቸውን በነፃ የገለፁ ወጣቶች በምንም መስፈርት በሕግ ሊጠየቁ የሚችሉበት አውድ እንደሌለ የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹ የሃይል እርምጃ ሲወስዱ እጅ ከፍንጅ እስካልተያዙ እና የአመጽ ጥሪ በይፋ እስካላስተላለፉ ድረስ፣ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልፁ የሚከለክላቸው ሕግ እንደሌለ ባለሙያዎቹ አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡ በእለቱ የነበረው እንቅስቃሴ በሙሉ በቪዲዮ ተቀርጾ የሚገኝ እንደሆነና፣ በአንዱም ላይ ለእስር እና ለምርመራ የሚዳርግ ጭብጥ እንደሌለው የሕግ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ እስሩ የሕግ ሳይሆን የጉልበት መሆኑን እያስረዱ ይገኛሉ ብሏል ባልደራስ በማህነራዊ ትስስር ገጹ።

Source: Link to the Post

Leave a Reply