የአድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን አንድነትና ኢትዮጵያዊ እሴት ለመመለስ ቃል እየገባን መሆን አለበት – ዶክተር ሙሉ ነጋ

የአድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን አንድነትና ኢትዮጵያዊ እሴት ለመመለስ ቃል እየገባን መሆን አለበት – ዶክተር ሙሉ ነጋ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን አንድነት፣ ሕብረትና ኢትዮጵያዊ እሴት ወደ ቀደመው ለመመለስ ቃል እየገባን መሆን አለበት ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ አሳሰቡ፡፡

125ኛው የአድዋ ድል በዓል በመቀሌ በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡

በፓናል ውይይቱ ዶክተር ሙሉ ነጋን ጨምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና ከድር፣ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ አድዋ ለዛሬው ትውልድ ከቀደምት ጀግኖች አባቶችና እናቶች የተሰጠ ለዛሬ ኃይል ፣ለነገ ደግሞ አቅምና የአሸናፊነት ስንቅ ጭምር መሆኑ ተገልጿል፡፡

የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊ አንድነትና ሕብረት የታየበት መሆኑም ተነስቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ በወቅቱ እንደተናገሩት÷የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን የነጻነት፣ የአንድነት እና የአልገዛም ባይነት ተምሳሌት ነው።

የአድዋ ድል በዓል ሲከበር የተሸረሸረውን የኢትዮጵያዊያን የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴት ለመመለስ ቃል በመግባት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያዊያን 125ኛውን የአድዋ ድል በዓል ስናከብር በክልል፣ በጎሳና በማንነት ሳንከፋፈል በአንድነት ስሜት መሆን ይኖርበታል ነው ያሉት።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዜና ከድር በበኩላቸው÷ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት ተሰባስበውና ኅብረታቸውን አጠናክረው ወራሪውን ጠላት ድል ያደረጉበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጀግኖች አባቶችና እናቶች የአድዋን ድል ሲቀዳጁ ለአገራቸው መስዋዕት ለመሆን ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ አልነበረም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ የአሁኑ ትውልድ ለአገሩ መልካም ሥራ በመስራት የራሱን ታሪክ ማስመዝገብ እንዳለበት መክረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም የአድዋ ድል ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካዊያን ሁሉ የማሸነፍ ስነ ልቦናን ያጎናጸፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዓሉ ሲከበር የአባቶችን ኅብረት፣ አንድነትና አገራዊ ፍቅር በማሰብና ያንን በተግባር ለማሳየት ቃል በመግባት መሆን እንዳለበት ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

The post የአድዋን ድል ስናከብር የተሸረሸረውን አንድነትና ኢትዮጵያዊ እሴት ለመመለስ ቃል እየገባን መሆን አለበት – ዶክተር ሙሉ ነጋ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply