የአጥንት እና አደጋ ስፔሻሊስት እና የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር ቃልአብ ተስፋዬ ጋር ስለ የአጥንት/ወገብ/ ቲቢ ከተደረገ ቃለ መጠይቅ የተወሰደ፤የአጥንት ቲቢ/የወገብ…

የአጥንት እና አደጋ ስፔሻሊስት እና የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር ቃልአብ ተስፋዬ ጋር ስለ የአጥንት/ወገብ/ ቲቢ ከተደረገ ቃለ መጠይቅ የተወሰደ፤

የአጥንት ቲቢ/የወገብ ቲቢ/ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ፤ከሳምባ በመቀጠል የሚሰከት የቲቢ ህመም ዓይነት ነዉ፡፡

ከሳምባ ዉጪ በመከሰት 15 በመቶ የሚሆነዉ የቲቢ ዓይነት ‹‹የአጥንት ቲቢ›› ነዉ ፡፡

#ምልክቶቹ ምንድናቸዉ?

ከሳምባ ቲቢ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ምልክቶች አሉት፡፡
ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት
ሌሊት ላይ በላብ መዘፈቅ
የድካም ስሜት
የክብደት መቀነስ
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
የወገብ ህመም የመጀመሪያ ምልክቶች ናቸዉ፡፡

#እነዚህ ምልክቶች መታከም ካልቻሉ ታዲያ ምን ይከሰታል?

የአጥንት አከርካሪ አጥንቶችን ያጠቃል/ዲስክ የማጥቃት ባህሪ የለዉም/
በዙሪያዉ ያሉ አካላት በመግል መሞላት ይጀምራሉ ፤ ይህም የነርቭ ዘንግን መጫን ያመጣል፡፡
ስለዚህ እግር መድከም ይጀምራል፣ የስሜት መቆጣጠር አለመቻል፣ ሽንት ሰገራን መቆጣጠር አለመቻልን ያስከትላል፡፡
ሌላኛዉ ምልክት ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ሊበላ ይችላል፡፡ ከአንድ በላይ የሆኑ የአከርካሪ አጥንቶች ሲበሉ ደግሞ ወደ መጉበጥ ይኬዳል፡
ያልታከመ ቲቢ አልያም ከታከመ በኋላም ጠባሳ ያለዉ ቲቢ ሰዉየዉ እንዲጎብጥ በተለይ ደግሞ ህጻናት ላይ መጉበጥ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡

#ምክንያቱ ምንድነዉ?
በአየር የሚተላለፍ የቲቢ መሰራጨት ለአጥንት ቲቢ ምክንያት ነዉ፡፡

#ይተላለፋል ወይ?

የሳምባ ህመምተኞች አክታቸዉ ዉስጥ የቲቢ ባክቴሪያ ስላለ ሊተላለፍ ይችላል፤ ብዙዎቹ የሳምባ ምልክት ስለሌለባቸዉ እና ሳልም ስለማይኖራቸዉ ግን የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነዉ ፡፡
የሳምባ ምልክት ያለባቸዉ ከሆኑ ግን የመተላለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነዉ፡፡

#ቅድመ መከላከል ማድረግ ይቻላል?

አብዛኛዉ የአጥንት ቲቢ ታማሚዎች የበሽታ የመከላከል አቅማቸዉ የወረደ ነዉ ፡፡
ህጻናት፣የምግብ ዕጥረት ያለባቸዉ፣ የኤችአይቪ ታማሚዎች፣ የካንሰር ታማሚዎች፣የስኳር ታማሚዎች፣ ስቴሮይድ ዓይነት መድሃኒቶችን የሚወስዱ ፣ የበሽታ መከላከል አቅምን ሊቀንሱ የሚችሉ መድሃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች የመጠቃት ዕድላቸዉ ከፍ ያለ ነዉ ፡፡

ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ መስጠት፣ ሌሎች ታማሚዎች ደግሞ አስፈላጊዉን መድሃኒት በአግባብ እና በጊዜ መዉሰድ አስፈላጊ ነዉ፡፡
የበሽታ መከላከል አቅም ያላቸዉ ሰዎች ግን የመያዝ ዕድላቸዉ ዝቅተኛ ነዉ ፡፡ በስፖርት፣ በአመጋገብ የበሽታ መከላከል አቅማችንን መገንባት እንደ ቅድመ መከላከል ሊወሰድ ይችላል፡፡

የበሽታ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረጉ ወሳኝ ጉዳይ ነዉ ፡፡
የበሽታ መከላከልን ሊያወርዱ የሚችሉ እንደ ሲጋራ ማጬስ፣ አልኮል መጠጣት ያሉ ተግባራትን ማቆም አልያም መቀነስም አስፈላጊ ነዉ፡፡
ቤት ዉስጥ ያሉ ቤተሰቦች ደግሞ ህመምተኛዉ የሳምባ ምልክቶችን የሚያሳይ ከሆነ ማስክ በማድረግ መከላከል ያስፈልጋል፡፡

#ህክምናዉ

ያለ ቀዶ ህክምና መታከም ይችላል፡፡
ከሳምባ ቲቢ በበለጠ መድሃኒት መዉሰድ ያስፈልጋል ፡፡ ከ10 ወራት እስከ 1 ዓመት ለሚሆን ጊዜ መድሃኒት መዉሰድን ይጠይቃል፡፡
ህጻናት ላይ ተከስቶ ከሆነ እና ብዙ የአከርካሪ አጥንትን ካጠቃ ሊያጎብጣቸዉ ስለሚችል ይህ ቀዶ ህክምና ያስፈልገዋል፡፡

ሌላኛዉ ደግሞ የተከሰተዉ መግል የእግር መስነፍ እና ፓራላይዝ ማድረግን ካመጣ የግድ ቀዶ ህክምና የሚያስፈልገዉ ይሆናል፡፡
ከዛ ዉጪ ያሉት የቲቢ ዓይነቶች ግን በጸረ ቲቢ መድሃኒቶች በአግባቡ መታከም የሚችሉ ናቸዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ

መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply