የአጥንት እና አደጋ ስፔሻሊስት እና የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር ቃልአብ ተስፋዬ ጋር ስለ የታችኛዉ አከርካሪ ዲስክ መንሸራተት ከተደረገ ቃለ መጠይቅ የተወሰደ#ዲስክ…

የአጥንት እና አደጋ ስፔሻሊስት እና የአከርካሪ ቀዶ ጥገና ሰብ-ስፔሻሊስት ከሆኑት ከዶ/ር ቃልአብ ተስፋዬ ጋር ስለ የታችኛዉ አከርካሪ ዲስክ መንሸራተት ከተደረገ ቃለ መጠይቅ የተወሰደ

#ዲስክ ምንድነዉ?

፤በአከርካሪ አጥንቶች መካከል የሚገኝ በፈሳሽ የተሞላ እና ዙሪያዉን በጅማት የተያያዘ ሲሆን፤ወገባችን እንዲታጠፍ እና ቀና ጎንበስ ማለት እንድንችል የሚያደርገን የአከርካሪያችን አካል ነዉ፡፡

#የዲስክ መንሸራተትስ?

፤ይህ በፈሳሽ የተሞላ ዲስክ ቦታዉን ለቆ ወደ ነርቭ መተላለፊያ ቱቦ በመግባት የነርቭ ዘንጎችን በሚጫንበት ጊዜ የሚፈጠር ህመም ነዉ፡፡

ስንት ዓይነት የዲስክ መንሸራተቶች አሉ?
፤የተለያዩ ዓይነት የዲስክ መንሸራቶች አሉ፤ የታችኛዉ ወገብ የዲስክ መንሸራተት፣ የአንገት ላይ የዲስክ መንሸራተት የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡
፤በጣም የተለመደዉ ዓይነት የዲስክ መንሸራተት ግን የታችኛዉ ወገብ የዲስክ መንሸራተት መሆኑን ባለሙያዉ ይገልጻሉ፡፡

#መነሻ ምክንያቶች?

፤ከባድ ስራ መስራት፣ አደጋ፣ የመዉደቅ፣ የመኪና አደጋ እንዲሁም ደግሞ ዕድሜ ሲገፋ የጸጉር መሸበት ፣ የቆዳ መሸብሸብ እንዳለ ሁሉ ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣ የዲስኮች መበላትም ሌላዉ ምክንያት ነዉ፡፡

#ተጋላጭ የሚሆኑት እነማን ናቸዉ?

፤ከባድ ስራ የሚሰሩ ወጣቶች ላይ በይበልጥ ይከሰታል፡፡
፤ስፖርተኞች ፣የረጅም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ከባድ ስራ የሚሰሩ የቀን ሰራተኞች ፣የኮንስትራክሽን ሰራተኞች በይበልጥ ተጋላጭ ናቸዉ፡፡ ከባድ ስራ ሲኖር ዲስካችን ላይ የሚያደርሰዉ ጫና ስለሚጨምር ዙሪያዉን የያዘዉ ጅማት ተበጥሶ መሃል ላይ ያለዉ ፈሳሽ ወደ ዲስካችን እንዲፈስ ያደርገዋል፡፡
፤አከርካሪ ላይ ከባድ ጫና የሚያሳድር ስራ መስራት ለመነሻ ምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡

#ምልክቶቹ ምንድናቸዉ?

፤ከታችኛዉ ወገብ ጀምሮ እስከ እግር ድረስ የሚሄድ ህመም
፤ከወገብ ጀምሮ መቀመጫ ላይ በአንድ በኩል የሚሰማ ህመም
፤ከታፋ ደግሞ በጀርባ በኩል የሚወርድ ከባድ ህመም
፤ብዙ ጊዜ የዲስክ መንሸራተት ከጉልበት በታች ይወርዳል በተለይ በባት በኩል ያለዉ ህመም እስከ እግር ጣቶች የሚሰማ የመደንዘዝ፣ የማቃጠል ፣የመንዘር ፣ የመዉረር እና የመጠቅጠቅ ስሜት ሊሰማ ይችላል፡፡
፤እነዚህ ምልክቶች የሚባባሱት ታዲያ ህመምተኛዉ ወገቡ በሚታጠፍበት ጊዜ ነዉ፡፡ መቀመጥ አይችልም፣ መቆምን ይመርጣል፡፡
፤ወገብ በሚታጠፍበት ጊዜ የተጫኑት ነርቮች መሳሳብ ስለማይችሉ መቆም እንጂ መታጠፍም ሆነ መቀመጥ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሲራመዱም ህመም በሌለበት በኩል ጋደል የማለት አዝማሚያ ይታያል፡፡ እነዚህ የተለመዱ ዓይነት ምልክቶች ናቸዉ፡፡

#ያልተለመደ ዓይነት የዲስክ መንሸራተት ምልክቶች የትኞቹ ናቸዉ?
፤ሁለቱ ወይም አንዱ እግር መዛል/ፓራላይዝ/ ዓይነት ስሜት ካለዉ
፤የሰገራ መዉጫ ፊንጢጣ አከባቢ የመደንዘዝ ስሜት ካለ
፤ሽንት እና ሰገራን መቆጣጠር ካልቻለ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋም መሄድ ያስፈልጋል፡፡
፤ይህ ምልክት ድንገተኛ የሆነ ቀዶ ህክምና እና ከፍተኛ የሆነ ትኩረት የሚፈልግ ነዉ፡፡

#ቅድመ መከላከል

፤ምክንያቶቹን ማስወገድ ፤አደጋን ማስወገድ ባይቻልም መቀነስ ይቻላል
፤በጣም መተጣጠፍ የሚያስፈልገዉ ዓይነት ስራ ከሆነ ወገባችንን መደገፍ ያስፈልጋል
፤ከመሬት ከባድ ዕቃዎችን ስናነሳ ተጎንብሰን ከምናነሳ ዝቅ ብለን በእግራችን ቁጢጥ ብለን ብናነሳ የተሻለ ይሆናል
፤ቤት ዉስጥ ከባድ ብረት የሚያነሱ ሰዎች ለወገባቸዉ ጥንካሬ የሚሰጡ ስፖርቶችን ቢሰሩ ድጋፍ ይሆናቸዋል
፤ከዛ በተጨማሪ አቀማመጣችን የተስተካከለ እና ቀጥ ያለ ቢሆን ይመከራል

#ህክምናዉ?

፤90 በመቶ የሚሆነዉ በራሱ አልያም በትንሽ ህክምና የሚድን ነዉ፡፡
፤ቀላል የሆኑ የወገብ ማጠንከሪያ እንቅስቃሴዎች፣ የነርቭ ህክምና፣ መድሃኒት ፣ የቁስለት መቀነሻ መድሃኒቶች በእነዚህ መዳን ይችላል፡፡እነዚህ ህክምናዎች ለ6 ሳምንት ይሞከራሉ፡፡
፤በዚህ ጊዜ ዉስጥ ህመሙ ካልቀነሰ ጀርባ ላይ በሚሰጡ መድሃኒቶች ህክምናዉ ይቀጥላል፡፡ ይህም ቁስለቱን የሚቀንስ ይሆናል፡፡ይህንን ህክምና አሁንም ለ6 ሳምንት ከፊዝዮቴራፒ ጋር በጋራ ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ ለ3 ወራት ጊዜ ያህል ያለ ቀዶ ህክምና ህክምናዉ ይሰጣል፡፡
፤ህመሙ ከፍ ካለ እና ሲጀምርም ሽንት እና ሰገራን መቆጣጠር የማይችሉ ከሆነ፣ ፊንጢጣ አከባቢ መደንዘዝ ካለ፣ እግር መዛል ፣ አለመታዘዝ ካለ ቀለል ባለ ቀዶ ህክምና ነርቩን የተጫነዉን ዲስክ በማዉጣት ህክምናዉ ይሰጣል፡፡

በእስከዳር ግርማ
የካቲት 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply